ዳግም የተወለደችው ከተማ

You are currently viewing ዳግም የተወለደችው ከተማ

“ይህ ፕሮጀክት የከተማችንን ብቻ ሳይሆን የሀገራችንን ገጽታ የሚቀይር ስኬት ሆኗል”
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ

አስተውሎ ለተመለከተው በእያንዳንዱ ሕንፃ ላይ ጸሐይ በምሽት የወጣች ይመስላል፡፡ በአረንጓዴ ዕፅዋት በታጀቡና እንደ ሙሽራ በተሽቆጠቆጡት መንገዶች ላይ ደግሞ የሰማይ ክዋክብት እንደ ስልጡን ሰራዊት በመልክ በረድፉ የተሰለፉበት ይመስል፤ ስፍራው ቀልብን ይማርካል፡፡

አንዱን ከአንዱ ማበላለጥ እስኪቸግር ድረስ ልማትና ደስታን የያዘ የውበት ጎርፍ በመዲናዋ መንገዶች ወዲህም ወዲያም ይወርዳል፤ ይነጉዳል፡፡

“አዲስ አበባማ ፣ አዲስ አበባማ፣

 ሽር ነው፣  . . . በጫማ” እንዳለው ዘፋኙ፤ በአዲስ አበባ የኮርደር ልማት ከተከናወነባቸው ቦታዎች መካከል 14ኛው መስመር በሆነው ከአትላስ ወደ ቦሌ ብራስ፣ ከቦሌ መድኃሊያለም እስከ ዓለም ሲኒማ ባለው መንገድ ከልቤም ከቀልቤም ተወዳጅቴ እየተገማሸርኩ ነው፡፡

እንኳንስ ተወቅራ፣ ሹርባ ተሰርታ፤

ድሮም አያስችለኝ፤ ፈገግ! ያለች ለታ፡፡ እንዲል የሀገሬ ሰው፣ በርካቶች በምድርም በሰማይም የሚከንፉባት የትናንቷ ፍልቅልቅ መንደር ቦሌ፣ በውበት ላይ ውበትን ደርባ ይበልጥ የምታሳሳ፣ የማትረሳም ሆናለች፡፡

በመንገዴ ላይ ነፍሱን ከፈጣሪው ሊያስታርቅ ወደ ቦሌ መድኃሊያለም እያመራ ያገኘሁት ወጣት ቢሊያም ልሳነ እንዳጫወተኝ፣ ከልጅነት እስከ እውቀት የቦረቀባት ሰፈሩ፣ ዓለም ሲኒማና አካባቢው በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ አስደማሚና ተስፋ ሰጭ ገፅታ መቀየሩ ገርሞታል፡፡

እጆቹን ወዲያና ወዲህ እያፈራረቀ “እዛ ….ጋ! በፊት እንዲህ ነበር፤ ይሄ ደግሞ እንዲያ፣ ዛሬ እንዲህ ማመሩ ያስደንቃል” እያለ፣ ቦታዎቹን በአካልም በምናብም ሲያስቃኘኝ በፊቱ ላይ የሚታየው ፈገግታ ደስታውን ከቃላት በላይ ይናገራል፡፡

በፊት የሚያውቃቸው ሕንፃዎች አዲስ እንደተገነቡ ያህል ተለውጠዋል፡፡ መንገዶቹ ከመስፋታቸው ባሻገር በአረንጓዴ ዕፅዋትም ታጅበዋል፡፡ በዳርና በዳር ከተተከሉት የመብራት ምሶሶዎች የሚወጣው ብርሃን ከመንገዶቹና ከአካባቢው ቀለማት ጋር ተወዳጅቶ የሚፈጥረው ድምቀት ምሽቱን ወደቀን ለውጦታል፡፡ እየጨለመ ሳይሆን ጎህ እየቀደደ፣ አዲስ ቀንም እየመጣ ይመስላል፡፡ እናም ቦሌ እየኖረባት እንደ አዲስ እንደምትናፍቀው ወጣት ቢኒያም አጫውቶኛል፡፡

የመዲናዋ  የሰማይ ላይ መግቢያና መውጫ በር፣ የልማት፣ የቱሪዝም እና የዲፕሎማሲ  ማዕከል የሆነው ቦሌና አካባቢው በርግጥም በኮሪደር ልማት ለብዙዎች የዐይንም የልቦናም ማረፊያ ሆኗል፡፡ ከአዲሶች አዲስ መሆኑን መነሻ በማድረግ ቦሌና አካባቢውን ለአብነት ጠቀስኩ እንጂ ከተማዋ በኮሪደር ልማት ሁለንተናዋን አስውባ እንደ አዲስ ከተወለደች ሰነባብታለች፡፡

አዲስ አበባ ድንገት የክት ልብሷን ከሳጥኗ መዥረጥ አድርጋ የአዘቦት ቀን ጉስቁልናዋን አራግፋ ሽቅርቅር እንደምትል የገጠር ሳዱላ! ከምኔው ያደፈ ሸማዋን አሽንቀንጥራ ጥላ የብርሃን ጸዳልን እንደተጎናጸፈች እንኳን ለእንግዳው ቀርቶ አብሯት ለሚኖረው ግርምትን የሚፈጥር መሆኑን ብዙዎች በመመስከር ላይ ናቸው፡፡

ከዝግጅት ከፍላችን ጋር ቆይታ ያደረጉት የከተማ ልማት ባለሙያው ኢንጅኒየር በሱፈቃድ አየለ እንደሚሉት ተስፋ የደራረቀውን የሰውን ልጅ ሕይወት እንደሚያለመልም ሁሉ ከተሞችም በልማት እንደ ንስር ይታደሳሉ፡፡ እንደ አዲስም ይወለዳሉ፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአዲስ አበባ የታውም ይህ ነው፡፡ ታሪክ፣ ቅርስንና ዘመናዊነት የተጣጣሙበት፣ ሰው፣ ሕንፃና ተፈጥሮ የተወዳጁበት የከተማ ልደት ነው፡፡ ይህ የአዲስ አበባ ለውጥ ስምና ምግባርም የገጠሙበት እውነት ነው፡፡

የከተማዋ አዲስ ለውጥ የዐይን ማረፊያ ብቻ ሳይሆን መንፈስንም የሚያጣፍጥ የልቦና ጨውም ነው፡፡ ሰዎች በኑሯቸው ደስተኛ እንዲሆኑ፣ ድህነትና መገለጫውን አሽቀንጥሮ ጥሎ ሰርቶ በመለወጥ እንዲህ ማማር ይቻላል! የሚለውን ወኔ በልቦናቸው ተክለው ለሁለንተናዊ ልዕልና እንዲነሳሱ የሚያደርግ ነው፤ ብለዋል የከተማ ልማት ባለሙያው ኢንጅኒየር በሱፈቃድ አየለ፣ የከተሞች ለውጥ ከነዋሪዎች ሕይወት ጋር ምን ተዛምዶ አለው? ስንል ላቀረብንላቸው ጥያቄ በሰጡን ምላሽ፡፡

ነዋሪዎች ከተሞቻቸውን ይመስላሉ የሚሉት  የከተማ ልማት ባለሙያው፣ በዘመናዊና በተለወጡ ከተሞች የሚኖሩ ሰዎች ጤናማ፣ ደስተኛ፣ ንቁና በሁለንተናዊ መልኩ የተሻሉ ናቸው፡፡ በዚያው ልክ ንፅህናቸው ባልተጠበቀ፣ በዘመን መግፋት፤ በአስታዋሽ ማጣት ባረጁና በተጎሳቆሉ ከተሞች የሚኖሩ ሰዎች እንደ ከተሞቻቸው ኑሮና ገፅታቸው የተጎሳቆለ ይሆናል፡፡ ስለዚህ የአዲስ አበባ ዳግም ልደት ለነዋሪዎቿም የተስፋ፣ የደስታና የመለወጥ ብርታትን የሚያጎናፅፍ ነው፡፡

ጥሩ ከተማ ማለት ሰዎች በቀላሉ የሚንቀሳቀሱበት እና የሚኖሩበት ነው፡፡ አዲስ አበባም በኮሪደር ልማት የተሸከርካሪ እና እግረኛ መንገዶችቿ ሰፍተውና ተውበው፣ የመዝናኛና አረንጓዴ ስፍራዎቿ ከፍ ብለው፣ የንግድና ልዩ ልዩ የአገልግሎት መስጫዎቿ ዘምነው፣ ነባሮቹ የቱሪዝም መዳረሻዎች ታድሰው፣ አንድነት፣ እንጦጦ፣ ወዳጅነትን የመሳሰሉ ውብና አዳዲስ ፓርኮች እንዲሁም የሳይንስ ሙዚየም፣ የዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ የአብርሆት ቤተመፅሀፍን የመሳሰሉ የታሪክና የዘመናዊነት መግቢያ በሮች ተከፍተው ከተማዋን ይበልጥ የብዙሃን መናገሻ አድርገዋታል፡፡

አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዘመናዊነት መግቢያ በር፣ የአዲስ ገፅታ መስታወት ናት፡፡  የሁሉም መድመቂያና ተናፋቂ ማዕከል ስለመሆኗም ብዙዎች ይመሰክሩላታል፡፡ አዲስ አበባ በየዘመናቱ አዲስ እና አበባ እየሆነች ለተለያዩ ከተሞችም ልምዷን እና ስልጣኔዋን እያጋራች ስለመቀጠሏ ታሪክ ምስክር ነው፡፡

በተለይ በቅርቡ  ከተማዋን ከስልጡን የዓለማችን  ከተሞች  ተርታ ለማሰለፍ እየተሰሩ ባሉ የኮሪደር ልማቶች አዲስ አበባ በትክክልም አዲስም፣ አበባም እየሆነች መምጣቷን በቅርቡ የተከናወኑ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ታላላቅ ጉባኤዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡

የዝግጅት ክፍላችን በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች ተዘዋውሮ እንደተመለከተው እነዚያ ጭንቅንቅ ያሉ መንገዶች፣ ጣሪያቸው ያረጀ፣ ማገራቸው የላላ፣ ምሶሷቸው ያዘመመ፣ ባለ ላስቲክ ግድግዎች እና የደቀቁ ስፍራዎች በውብ መናፈሻዎች፣ በሰፋፊ መንገዶች እና በሰማይ ጠቀስ ህንፃዎች እየተተኩ ነው፡፡ በርግጥም አዲስ አበባ ገና ከጫጉላ ቤት እንደወጡ ሙሽሮች፣ እንደ ቀይ ሐር ፈትል፣ በለምለም መስክ ላይ እንደሚቦሩቁ እንቦሶች እና በስሎ ለሁለት እንደ ተከፈለ ሮማን ዐይንንም ልብንም እየማረከች ነው፡፡

የመዲናዋ ነዋሪ ወይዘሮ ምንትዋብ አስረስ እንደሚሉት ከተማዋ በርግጥም ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለልጆቻችንም ምቹ ሆና እየተሰራች ነው፡፡ አሁን ልጆቻችንን ወስደን የምናጫውትበት ቦታ አይቸግረንም፤ በየጎዳናዎቹ የመናፈሻ ስፍራዎችና እና ፏፏቴዎች እንዲሁም ልዩ ልዩ የልጆች መጫወቻዎች አሉ፡፡ እየተሰሩ ያሉ ልማቶችም በጣም ፅዱ በመሆናቸው ጤናችንን እየጠበቅን የተሻለ ሕይወትን ከቤተሰቦቻችን ጋር እንድንመራ ያስችላሉም ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት 4ኛ የሥራ ዘመን፣ 3ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ በአዲስ አበባ እየተከናወነ ያለውን ኮሪደር ልማት አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክትም በአዲስ አበባ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ፍትሐዊ ልማት ለዜጎቻችን ያቀረብንበት ነው ማለታቸው የሚታወስ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ትናንት ከኡራኤል – ቦሌ መድኃኔዓለም እስከ ቦሌ ቪአይፒ (VIP) ተርሚናል የሚያገናኘውን የኮሪደር ልማት መጠናቀቁን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክታቸው፣ “የከተማችን ተጨማሪ ድምቀት በሆነው ከኡራኤል – ቦሌ መድኃኔዓለም እስከ ቦሌ ቪአይፒ (VIP) ተርሚናል የሚያገናኘው የኮሪደር ልማት፣ ለአካባቢው ተጨማሪ ውበት የሚያጎናፅፉ እና ለሕዝብ ከፍተኛ ጥቅም ያላቸውን ዘርፈ-ብዙ ሥራዎች አካትተን አጠናቀናል” ብለዋል፡፡

ይህ መስመር ቀደም ሲል ደረጃቸውን ያልጠበቁ የአስፋልት መንገዶች፣ የእግረኛ መንገድ እጥረት፣ የሳይክል መንገድ አለመኖር እና ከፍተኛ የመኪና ማቆሚያ (ፓርኪንግ) ችግር የነበረበት እንደነበር ያስታወሱት ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች፣  በተጨማሪም ምንም ዓይነት የስፖርት ሜዳዎችም ሆኑ የሕፃናት መጫወቻዎች ያልነበሩበት፣ የህንፃዎች ውበት በቆሻሻና ዕድሳት በማጣት እንዲሁም አላስፈላጊ በሆኑ ተለጣፊ ግንባታዎች ተሸፍኖ የቆየ እንደነበር እና ዛሬ ግን በኮሪደር ልማቱ አካባቢው ለዐይን ማራኪና ዘመናዊ መልክ ይዟልም ሲሉም አክለዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ካካተታቸው ዋና ዋና ስራዎች መካከልም 5 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ፣ 60 ሜትር ስፋት ያለውና በሁለቱም በኩል 4 መስመሮችን የያዘ፤ የትራንስፖርት ተርሚናል፣ ዘመናዊ የታክሲና የአውቶቡስ ተርሚናሎች፣ 10 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የእግረኛ መንገድ (ከ5 እስከ 10 ሜትር ስፋት ያለው) እና 4 ኪሎ ሜትር የብስክሌት መስመር፣ በመንግሥትና በግለሰቦች ትብብር በአንድ ጊዜ እስከ 2 ሺህ መኪናዎችን (900 ከቤት ውጭ እና 1ሺህ 1መቶ በህንፃዎች ውስጥ) ማቆም የሚችሉ ስፍራዎችን የያዘ ነው፡፡

እንዲሁም 3 ሺህ 442 ነጥብ 38 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ የተሽከርካሪዎች ቻርጅ ማድረጊያ፣  15 የታክሲና አውቶቡስ ማቆሚያዎች፣ 8 ካፌዎች ከሕዝብ መጸዳጃ ጋር፣ ፕላዛዎች እና ለአነስተኛ ንግዶች የሥራ ዕድል የፈጠሩ ሱቆችን ያካተተ ሲሆን፣ 5 ፋውንቴኖችንም የያዙ ውብ አረንጓዴ ስፍራዎች፣ የእግር ኳስና የቅርጫት ኳስ ሜዳዎች እንዲሁም የሕፃናት መጫወቻ ስፍራዎችም እንዳሉት ተናግረዋል፡፡

አካባቢው ውበታቸው ተመልሶ የታደሱ ከ2 ሺህ በላይ ሕንፃዎች፣ በከፍተኛ ጥራትና ፍጥነት መሰራታቸውን የጠቀሱት የአዲስ አበባ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፣ እነዚህን ሁሉ አስደናቂ ተግባራት ሦስት ወራት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አጠናቅቀን ለሕዝብ አገልግሎት ክፍት በማድረጋችን ታላቅ ደስታ ይሰማናልም ብለዋል፡፡

አክለውም፣ ይህ ፕሮጀክት የከተማችን ብቻ ሳይሆን የሀገራችን ኩራት እና ገጽታን የሚቀይር ስኬት ሆኗል። ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም በላይ የንግድ እንቅስቃሴውን በእጅጉ አነቃቅቷል፤ ወደፊትም የተሻለ ውጤት እንደምናገኝበት ሙሉ እምነት አለን። ከእኛ ጋር በመሆን በትጋት የደከማችሁ አመራሮች፣ ሠራተኞችና ባለሙያዎች፣ በ24/7 የሥራ ባሕል ቀንና ሌሊት የለፋችሁ ሁሉ ምስጋና ይገባችኋል። እንዲሁም በመስመሩ ላይ ያላችሁ ባለሀብቶች፣ ነጋዴዎች፣ የቤትና የሕንፃ ባለቤቶች ሌት ተቀን ከጎናችን በመቆም ላደረጋችሁት ከፍ ያለ ትብብርና ማበረታቻ ምስጋናችን የላቀ ነው በማለትም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ካፕሽን፡- ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እና ከፍተኛ አመራሮች ከአትላስ ወደ ቦሌ ብራስ፣ ከቦሌ መድኃሊያለም እስከ ዓለም ሲኒማ ባለው መንገድ የተከናወነውን የኮሪደር ልማት በጎበኙበት ወቅት

በ2ኛው ዙር የኮሪደር ልማት ስራ አዲስ ገፅታ የተጎናፀፈው ከአትላስ ወደ ቦሌ ብራስ፣ ከቦሌ መድኃሊያለም እስከ ዓለም ሲኒማ ያለው መንገድ ከፊል ገፅታ

በመለሰ ተሰጋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review