በቴክኖሎጂ የተደገፈው አሰራር ምን ውጤት እያመጣ ነው?

You are currently viewing በቴክኖሎጂ የተደገፈው አሰራር ምን ውጤት እያመጣ ነው?

በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ 6 ወራት ለ805 ሺህ 432 ነዋሪዎች የነዋሪነት አገልግሎት ተሰጥቷል

አስቴር ለገሰ ይባላሉ፡፡ ከዚህ ቀደም ነዋሪነታቸውን በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 አድርገው የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ የመኖሪያ አድራሻቸውን ወደ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ቀይረዋል፡፡ እኛ ያገኘናቸው፣ ያላገባ ምስክር ወረቀት (ሰርተፍኬት) ለማውጣት ወደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ መጥተው ነው፡፡ ስለ አገልግሎቱ ጠይቀናቸው በሰጡት አስተያየት፤ “ገና ወደ ቅጥር ግቢው እንደገባሁ መንፈስን የሚያድስ የሥራ ከባቢ ለማየት በመቻሌ ደስ ብሎኛል፡፡ የያዝኩትንም ጉዳይ አምስት ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አጠናቅቄ ወጥቻለሁ፡፡ ከዚህ ቀደም ኩነት ነክ ጉዳዮችን ለማስፈጸም ብዙ ምልልሶች ነበሩ፡፡ አሁን ግን አሠራሩ ተሻሽሏል። ቲኬት ቆርጠን ወረፋ እንይዛለን፡፡ በዚያ መሠረት አገልግሎት ወደሚሰጡ መስኮቶች ቀርበን እንስተናገዳለን፡፡ ከእኛ የሚጠበቀው ነገር ተገቢውን መረጃ ብቻ ይዘን ወደ ተቋሙ መምጣት ነው” ብለዋል፡፡

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 14 ነዋሪ የሆኑት አቶ ዮሐንስ አበጀ በበኩላቸው ወደ ሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ የመጡት በክብር መዝገብ ሹም ፊት የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ለመከወን ነው፡፡ ስለ አገልግሎት አሰጣጡ በሰጡት አስተያየት፤ አስፈላጊ የሚባሉ ቅድመ ሁኔታዎችን እንዲያሟሉ መረጃ እንደተሰጣቸው በመግለጽ፣ ያገኙትን ግንዛቤ ለሌሎች እንደሚያካፍሉ ገልጸዋል፡፡

የጋብቻ ምስክር ወረቀቱን ለመቀበል ያለፉባቸው ሂደቶችና የተስተናገዱበት አግባብ በቴክኖሎጂ የተደገፈ መሆኑ እጅግ እንዳስደሰታቸው የተናገሩት አቶ ዮሐንስ፤ “ከዚህ ቀደም ወረዳ ላይ የምንስተናገድበት መንገድ ግልጽ ያልሆነ ብሎም ለብልሹ አሠራር የተጋለጠ ነበር” ይላሉ፡፡ ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረገ የአሠራር ሥርዓት መከተል አካሄዱን ግልጽነት የተላበሰና ፍትሐዊ እንዲሆን እንደሚያደርገውና እሳቸውም መረጃቸው ከሁለት ደቂቃ ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ወጥቶላቸው መስተናገዳቸውን አብራርተዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ ሐሳብና አስተያየት እንዲሰጡን በአዲስ አበባ ሲቪል ምዝገባና የነዋሪዎች አገልግሎት ኤጀንሲ ውስጥ የኩነት ማረጋገጫ ባለሙያ የሆኑትን አቶ መስፍን ንጉሡን ጠይቀናቸዋል። እሳቸው እንዳስረዱት፤ ለተገልጋዮች አገልግሎት ለመስጠት በቅድሚያ የተለያዩ መረጃዎችን የማረጋገጥ ሥራ ይሠራል። ግለሰቦች ከተለያዩ ተቋማት ማረጋገጫ እንዲያመጡ በሚጠየቁበት ወቅት እንደ ልደት፣ የጋብቻ፣ የፍቺ፣ ያላገባ እንዲሁም ያገባ ማስረጃዎችን የማረጋገጥ ሥራ ይከናወናል፡፡ አዲስ አበባ ላይ በሚገኙ 122 ወረዳዎች የተሰበሰቡ ማስረጃዎችን የማረጋገጡ ሂደት በተለመደው ማንዋል አሠራር ማከናወን በጣም አድካሚና ለስህተትም የሚዳርግ ነው፡፡ ስለዚህ አገልግሎቱን በተቀላጠፈ መንገድ ለማስቀጠል ቴክኖሎጂን መጠቀም መቻሉ ችግር ፈቺ የአሠራር ሥርዓትን ይዞ እንደመጣ አስታውቀዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ1935 ዓ.ም እስከ 2001 ዓ.ም ያሉት በማዘጋጃ ቤት የተመዘገቡ ኩነቶች ፋይላቸው በአዲስ አበባ ሲቪል ምዝገባና የነዋሪዎች አገልግሎት ኤጀንሲ እንደሚገኝ ያነሱት አቶ መስፍን፤ ኤጀንሲው እነዚህን መዝገቦች የማረጋገጥ ሥራ እንደሚሠራ አስረድተዋል፡፡ በዚህ ሥራ ላይ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ወረቀት አልባ አገልግሎቶችን መስጠት መቻሉ የግለሰቦች ፋይል እንዳይጠፋ ያግዛል። በተለይም ጊዜን ቆጣቢ ብሎም ሰዎች የሚያደርጓቸውን ምልልሶች ከማስቀረት አንጻር ሁነኛ መፍትሔን አበጅቷል ብለዋል፡፡

 እንደ አዲስ አበባ ከተማ፣ የስማርት ሲቲን ፅንሰ ሐሳብ በተግባር ለመከወን የሚያስችል የዘመነ የአሠራር ሥርዓት መከተል በሚያስችለን ጎዳና ላይ እንደሚገኙ በመጠቆም ለዚህ የሰርግ ኩነት ምዝገባን እንደማሳያ አንስተው አብራርተዋል፡፡

ጋብቻ ስለመፈጸሙ በመረጃ የታገዘ ምዝገባ ይካሄዳል” የሚሉት ዳይሬክተሯ፣ ከሁለቱ ሙሽሮች አንዳቸው በቅድሚያ የመኖሪያ መታወቂያ ባወጣበት/ችበት ቦታ ላይ ማመልከቻ ያስገባል/ለች፡፡ ከዚያም ለ15 ቀናት አየር ላይ የሚውል ደብዳቤ በወረዳው በኩል ይለጠፋል፡፡ ተቃዋሚ መጥቶ “ባለቤቴ ነች፤ ወይም ባለቤቴ ነው” የሚል ከሌለ ጋብቻቸው በክብር መዝገብ ሹም ፊት ይጸድቃል፡፡ ተጋቢዎቹ በሁለቱም ወገን ሁለት ሁለት ምስክሮችን ይዘው ይቀርባሉ፡፡ የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ ካርድ እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ የነዋሪ መታወቂያ ካርድ ይዘው መምጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የተሟሉትን መረጃዎች የሚመለከተው ባለሙያ ካጣራ በኋላ የጋብቻ ምስክር ወረቀታቸው ታትሞ ይሰጣቸዋል፡፡ ከዚያም መረጃውን በቴክኖሎጂ የተደገፈ በማድረግ ሲስተም ላይ ይጫናል ሲሉ አብራርተዋል፡፡

እንደ ወይዘሮ ቤዛዊት ገለጻ፤ በቴክኖሎጂ የታገዘው የአሠራር ሥርዓት ሰዎች በቀላሉ የተለያዩ ቦታዎች የጋብቻ ምስክር ወረቀት እንዳያወጡ ያደርጋቸዋል፡፡ በቀላሉ ሲስተም ላይ የሚጫኑ መረጃዎች እስከ ማዕከል የሚደርሱ በመሆኑ ለማንም ለሕገ-ወጥ ተግባራት ዕድል አይሰጥም፡፡

የጋብቻ እንዲሁም ሌሎች ኩነቶችን ለመመዝገብ በሚደረገው ጥረት በሁሉም ወረዳዎቻችን ላይ አገልግሎቶችን በስፋት መስጠት ይቻል ዘንድ ከዚህ ቀደም በመብራትና በሲስተም መቆራረጥ ይቸገሩ የነበሩ ቁጥራቸው 22 የሚሆኑ ወረዳዎች የሶላር ኢነርጂ ተገጥሞላቸው ሥራቸውን በተቀላጠፈ አግባብ እየከወኑ ይገኛሉ፡፡ የኔትዎርክ ችግርን ለመቅረፍ እንዲሁ ከቴሌ ጋር በጋራ በመሆን ችግሮች ሲገጥሙ በቀላሉ በስልክ መልእክት ለመለዋወጥ ያስችል ዘንድ በየወረዳው ከሚገኙ የተቋሙ የኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ባለሙያዎች ጋር የቅርብ ግንኙነት እየተደረገ መሆኑን የሚናገሩት ዳይሬክተሯ፣ ከዚህ ቀደም ሲመዘገብበት የነበረው ሲስተም ካለው የከተማዋ ሕዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ አቅሙን ከፍ ማድረግን ይጠይቅ እንደነበር አስታውሰዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወራት ሪፖርትም ይህንኑ የሚያጠናክር ነው፡፡ ይህንኑ የዕቅድ አፈጻጸም በቅርቡ ለአዲስ አበባ ምክር ቤት አባላት ያቀረቡት ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፣ የሲቪል ምዝገባና ነዋሪነት አገልግሎቶች ደረጃና ተደራሽነትን ለማሻሻል ከዚህ በፊት ለረጅም ጊዜ አገልግሎት ይሰጥ የነበረውንና ለተገልጋይ እንግልት ምክንያት የሆነውን የሲስተም መቆራረጥ ችግር መፍታት የሚያስችል አዲስ ሲስተም በማልማት ወደ ሥራ ማስገባት ተችሏል፡፡ ለ805 ሺህ 432 ነዋሪዎች የነዋሪነት አገልግሎት መስጠት የተቻለ ሲሆን በቀጣይም ለበለጠ ውጤታማነት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ ተናግረዋል።

ኩነቶችን በወቅቱ በማስመዝገብ ሁሉም የአዲስ አበባ ነዋሪ ድርሻውን ሊወጣ ይገባል፡፡ በተለይም የኤጀንሲው ባለድርሻ አካላት የሚባሉት እንደ ጤና ተቋማት (የልደት ምዝገባ)፣ የአዲስ አበባ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ (የሞት ምዝገባ)፣ መደበኛ ፍርድ ቤቶች እንዲሁም የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች (የጋብቻና ፍቺ ምዝገባ) ምዝገባዎችን በተቀላጠፈ መንገድ እንዲከወኑ እያደረጉት ያለውን እገዛ አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡

በሄለን ጥላሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review