የአስጎብኚዎች የአምባሳደርነት ሚና

የቱሪስት መስህቦችን ከማልማት እና መሠረተ ልማቶችን ከማሟላት ባልተናነሰ፣ የሚፈለገውን ያህል የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ቱሪስቶች እንዲጎበኟቸው ማስተዋወቅ ውዴታ ሳይሆን ግዴታ ነው። አዲስ አበባ በዘርፉ ካላት የመሸጋገሪያነት ሚና ወደ መዳረሻነት ትቀየር ዘንድ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተሰሩ ሥራዎች በአይነት የሚታዩ፣ የቱሪስቶችን ምስክርነትም ያገኙ ናቸው፡፡ በተለይ በማስተዋወቅ ሥራው ከዚህም በላይ መሥራት ይጠበቃል። ለዚህ ደግሞ አስጎብኚዎች በሁሉም መልክ የበቁ እንዲሆኑ ማድረግ የግድ ይላል፡፡

አቶ ጌታቸው ሆፎላ የአዲስ አበባ ቱሪስት አስጎብኚዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ናቸው፡፡ ከ15 ዓመት በላይ የማስጎብኘት ልምድ አላቸው፡፡ ቱሪስቶች ኢትዮጵያን፣ በተለይ ደግሞ እንደ ስሟ አዲስ የሆነችውን አዲስ አበባን በሚፈልጉት ልክ አውቀዋትና ተዝናንተው፣ እንዲሁም በሚያወጡት ወጪ ልክ አገልግሎት አግኝተው ይመለሱ ዘንድ የአስጎብኚዎች ሚና ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድ ይናገራሉ፡፡

አቶ ጌታቸው እንደሚናገሩት፣ አዲስ አበባ እየለማች፣ እየተዋበች፣ ቱሪስቶችን መሳብ እና የቆይታ ጊዜያቸውን እንዲያራዝሙ የሚያደርግ አቅም እየፈጠረች መጥታለች፡፡ ይህ የቱሪስት መዳረሻነቷ እያደገ መምጣት ደግሞ ለአስጎብኚዎች ትልቅ ዕድል ይፈጥራል፡፡

“ከዚህ በፊት ኢትዮጵያን ለመጎብኘት የሚመጡ ቱሪስቶች አብዛኛውን ጊዜ አዲስ አበባን ወደ ሌሎች የመዳረሻ ቦታዎች ለመሄድ እንደ መሸጋገሪያ ነበር የሚጠቀሟት፡፡ አሁን ግን በከተማዋ የተሰሩ አዳዲስ፣ ውብና ዘመናዊ ፓርኮችን፣ ሙዚየሞችን እንዲሁም ጎዳናዎችን እናስጎበኛቸዋለን፡፡ አዲስ ፕሮጀክት ሲመረቅ የጉብኝት ዝርዝራችን ውስጥ በማካተት ቱሪስቶችን ለማቆየት እና ከተማዋንም ራሳችንንም ለመጥቀም የሚያስችሉ ሥራዎችን እንሠራለን፡፡ በግሌም ተጨማሪ የማስጎብኘት ዕድል ፈጥሮልኛል” ይላሉ አቶ ጌታቸው፡፡

አቶ ጌታቸው በማብራሪያቸው፣ “ጎብኚዎች መርጠውን እንዲመጡ በኦንላይን አዳዲስና ነባር መዳረሻዎችን እናስተዋውቃለን፡፡ ይህንን የማስጎብኘት ዕድል ተጠቅመን ተገቢውን ሥራ ለመሥራት ከአየር ማረፊያ ወይም ደግሞ ከሆቴሎች ጀምረን አቀባበል እናደርጋለን፡፡ አዲስ አበባ (New Flower) የተባለችበትን ምክንያት እና መቼ እንደተቆረቆረች የማሳወቅ ሥራ እንሠራለን፡፡ ከዚያም እንደ ፍላጎታቸው እናስጎበኛቸዋለን፡፡ በዚህም ከኮሪደር ልማቱ በፊት የሚያውቋት ጎብኚዎች አሁን ላይ ከእንጦጦ ፓርክ ጀምሮ የኢትዮጵያ ኮሪያ ዘማቾች፣ አራዳ፣ ወዳጅነት፣ አምባሳደርና ፒኮክ ፓርኮችን እና ሌሎችንም የለሙ የወንዝ ዳርቻዎችን ሲጎበኙ፣ ይህ አዲስ አበባ ውስጥ የተከናወነ መሆኑን እስከሚጠራጠሩ ድረስ በጣም ይደነቃሉ፡፡ በዚህም ኩራት እየተሰማኝ ነው የማስጎበኘው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለጻ፣ ማህበሩ ከ200 በላይ አስጎብኚ አባላትን አቅፏል፡፡ እነዚህ አባላት የተለያዩ ቋንቋዎችን የሚችሉ ናቸው፡፡ እሳቸውም በእንግሊዝኛ፣ በአማርኛ እንዲሁም በኦሮምኛ ቋንቋዎች ጎብኚዎችን እየተቀበሉ ያስተናግዳሉ፡፡ ይህንን ዕውቀት የበለጠ ከፍ ለማድረግና ለጎብኚዎች ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል አቅም ለመፍጠር ከሌሎች አስጎብኚዎች ጋር የልምድ ልውውጥ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቱሪዝም መምህራንን በመጋበዝ የተለያዩ ሥልጠናዎችን እንዲሰጡና የማህበሩ አባላት ዕውቀት እንዲያገኙ እየተደረገ ነው፡፡

“በተለየ ሁኔታ በኮሪደር ልማቱ የለሙትን የወንዝ ዳር ልማትን፣ ፓርኮችንና መሰል አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በአግባቡ ማስጎብኘት እንዲቻል በአዲስ አበባ ከተማ ቱሪዝም ኮሚሽን ሥልጠናዎችን አግኝተናል፡፡ ወደፊትም የሚያስፈልጉ ሥልጠናዎችን ለማመቻቸት ኮሚሽኑ ቃል ገብቶልናል” ሲሉም ፕሬዝዳንቱ አብራርተዋል፡፡

አንድ አስጎብኚ “አስጎብኚ ነኝ” ለማለት ዕውቀት ሊኖረው እንደሚገባ የሚናገሩት ፕሬዝዳንቱ፣ “ስለምናስጎበኘው ቦታ እና ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ በደንብ አውቀን ሳናዛባ መናገር መቻል ይጠበቅብናል፡፡ ለዚህም እናነባለን፤ ለማወቅ እንጥራለን። እንደ ማህበርም በስብሰባዎች ላይ ማንኛውም አስጎብኚ ራሱን ማሻሻል እንዳለበት እንነጋገራለን” ብለዋል፡፡

ሽፈራው ሙለታ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቱሪዝም ልማትና አስተዳደር የትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚናገሩት፣ አዲስ አበባ የቱሪስት መዳረሻ ለመሆን በርካታ መዳረሻ ቦታዎችን አልምታለች። የተሰሩት ፕሮጀክቶች ለውበት ብቻም ሳይሆን በጎብኚዎች አዕምሮ ውስጥ መቀረጽ መቻል አለባቸው፡፡ ይህ ደግሞ የሚሆነው በአስጎብኚዎች ነው፡፡ እነዚህ አስጎብኚዎች አጠቃላይ ኢትዮጵያንም ሆነ የለማችውን አዲስ አበባን ለማስጎብኘት ስለ ቱሪዝም መዳረሻዎች ቀድሞ የማወቅና የማሳወቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡

እንደ ሽፈራው (ዶ/ር) ገለጻ፣ አስጎብኚዎች ለጎብኚዎች የጉብኝት ቦታዎችን በማስተዋወቅ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ራሳቸውን በዕውቀት ማሳደግ እና በየጊዜው ሥልጠናዎችን ማግኘት አለባቸው፡፡ ይህ ሲሆን ጎብኚዎች ማወቅ የሚፈልጉትን እንዲያውቁ፣ ደስተኛ እንዲሆኑ፣ የቆይታ ጊዜያቸውን እንዲያራዝሙ ብሎም ደግመው እንዲመጡ፣ ሀገራችንም ከቱሪዝም ማግኘት ያለባትን ገቢ እንድታገኝ ያስችላል፡፡

 በዚህም በአስጎብኚዎች የጉብኝት ፓኬጆች ውስጥ የትራንስፖርት፣ የማረፊያ ሆቴሎች፣ የሎጆች፣ የምግብ አገልግሎቶች እንዲሁም የሚጎበኙ ቦታዎችን የማሳወቅና በሚፈልጉት ቋንቋ የማስጎብኘት ድርሻቸው ላቅ ያለ መሆን እንዳለበትም አክለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን የቱሪዝም መዳረሻ ልማትና የሀገር ውስጥ ቱሪዝም ማስፋፋት ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን አይናቸው በበኩላቸው፣ “በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው ልማት የቱሪስት ተደራሽነቷን እንደጨመረው ነግረውናል። መሠረተ ልማቶችን በማዘመን፣ አዳዲስና ነባር የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማልማት፣ በማስዋብና ምቹ በማድረግ የቱሪስት መዳረሻ ማድረግ ተችሏል። በዚሁ ልክ አስጎብኚዎች የቱሪስት ቦታዎችን በማስተዋወቅና ለጎብኚዎች ተገቢውን መረጃ በመስጠት ከፍተኛ ኃላፊነት ይጠበቅባቸዋል፡፡ አስጎብኚዎች ዕውቀት ኖሯቸውና ከተማዋ ያለችበትን ሁኔታ ተገንዝበው መዳረሻ ቦታዎችን እንዲያስጎበኙ ኮሚሽኑ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎችን ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ ከአዲስ አበባ ኮሪደርና ወንዞች ዳርቻ ልማት አስተዳደር ባለሥልጣን የመጡ ባለሙያዎችም ሥልጠናዎችን እንዲሰጡ ተደርጓል” ብለዋል፡፡

ከሥልጠናዎች ባለፈ የተሰሩ ሥራዎችና መዳረሻ ቦታዎቹ ምን እንደሚመስሉም ከማስጎብኘታቸው በፊት እንዲጎበኙ ተደርጓል፡፡ ሁሉም አስጎብኚዎች በሕጋዊ ሥርዓት የኮሚሽኑን መታወቂያ ይዘው ሥራቸውን ማከናወን እንዲችሉ እየተሠራ እንደሚገኝም አክለዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ ቱሪስቶች ቀድመው የሚያገኟቸውና በርካታ መረጃዎችን የሚቀበሉት ከአስጎብኚዎች ነው፡፡ በዚህም ምክንያት አስጎብኚዎች የሀገሪቱም ሆነ የከተማዋ አምባሳደር ወይም ገጽታዎች ናቸው፡፡ አስጎብኚዎች አምባሳደር ናቸው ሲባልም በዕውቀት ከመታነጽ ባለፈ የአስጎብኝነት ሥነ ምግባር፣ እንግዳ ተቀባይነትና አክብሮትን መላበስ፣ ስለ ቅርሶችና መዳረሻዎች ታሪክ ትክክለኛና እውነተኛ መረጃን መስጠት፣ በሥራ ሰዓት አልኮል፣ ጫትና አደንዛዥ ዕፅ አለመጠቀም፣ ትዕግሥተኛ መሆን እንዲሁም ሕጋዊ መታወቂያ ይዞ መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ማንኛውም መዳረሻ ቦታዎችን የሚያሳይ ሰው አስጎብኚ አይደለም ያሉት አቶ ሳምሶን፣ አስጎብኚዎች ሕጋዊ ሥርዓት ኖሯቸው በዕውቀትና በጥበብ ከተማቸውንም ሆነ ሀገራቸውን ማስጎብኘት እንዲችሉ የአስጎብኚ ማህበራትን ለማጠናከር እንዲሁም ከኮሚሽኑ ጋር አብሮ ለመሥራት የሥራ ስምምነት መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በከተማዋ ያሉ የቱሪስት መዳረሻዎችን በዓለም ደረጃ ለማስተዋወቅ ከተማ አስተዳደሩ ለዚህ እንቅስቃሴ ይመጥናል ብሎ ያስገባቸው ስድስት የሚደርሱ ክፍት አውቶቡሶች አሉ፡፡ የወንዝ ዳርቻዎችን ለመጎብኘት የሚያስችሉ ትናንሽ ተሽከርካሪዎችንም እንዲሁ፡፡ እነዚህ የከተማዋን ገጽታ ከመገንባት አንጻር የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ዳይሬክተሩ አቶ ሳምሶን ያስረዳሉ፡፡

ኮሚሽኑም እንደ አንድ የቱሪዝም ተቋም ከተማዋን የሚመጥኑ የቱሪዝም መስመሮችን ለምሳሌ፡- ቱሪስቶች ሙዚየሞችንም ሆነ ፓርኮችን መጎብኘት ቢፈልጉ በየትኛው ሰዓት ሄደው መጎብኘት ይችላሉ? ግብይት ሲፈልጉ የት ቦታ ላይ ይገበያሉ? የሚሉትን የጉብኝት መስመሮች አዘጋጅቷል፡፡ የጉዞ አገልግሎቶችን በጥቅል አዘጋጅተው ለደንበኞች የሚያቀርቡት ደግሞ ቱር ኦፕሬተሮች ናቸው፡፡

ከከተማዋ መልማት ጋር ተያይዞ አስጎብኚዎች ስለ ከተማዋ እና ስለ ጎብኚዎች ዕውቀት ኖሯቸው እንዲያስጎበኙና ጎብኚውም የሚፈልገውን አውቆ ወይም ጎብኝቶ እንዲመለስ፣ ኮሚሽኑ የከተማ አስተዳደሩንና የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮን በማስፈቀድ 10 የሚሆኑ የተለያዩ ቋንቋዎችን የሚናገሩ አስጎብኚዎችን መቅጠሩን አቶ ሳምሶን ተናግረዋል፡፡

የእነዚህን ወጣት አስጎብኚዎች አቅም በመገንባት፣ በአካል ከተማዋ ውስጥ የተከናወኑትን የቱሪዝም ልማት እንዲያዩ በማድረግ የማስጎብኘት አገልግሎት የሚሰጡ ይሆናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የከተማዋን የቱሪዝም መዳረሻነት ለዓለም ለማሳወቅ ተሳትፎ የሚያደርጉ በጎ ፈቃደኞች አብረዋቸው እንደሚሰሩም ዳይሬክተሩ አክለዋል፡፡

በጥቅሉ በአዲስ አበባ በቅርብ ዓመታት ነባሮችን ከማደስ ባሻገር በርካታ ተፈጥሮን፣ ታሪክንና የሰው ልጅ ጥበብን ያወዳጁ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች ተገንብተዋል፤ በመገንባት ላይም ናቸው፡፡ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ከማልማት ጎን ለጎን በቱሪዝም ኢንዱስትሪ ዘርፍ ቁልፍ ሚና የሚጫወቱት አስጎብኚዎች ለቱሪስቶች አስፈላጊውን መረጃ በመስጠት፣ የከተማዋንና የሀገር አምባሳደርነት ሚናቸውን በብቃት እንዲወጡ ማድረግ ይገባል እንላለን፡፡

በፋንታነሽ ተፈራ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review