በመዲናችን አዲስ አበባ ባሳለፍነው ሳምንት የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች ለጥበብ አፍቃሪያን ሲቀርቡ ቆይተዋል። ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናትም መሰል መርሃ ግብሮች መቅረባቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ከተሰናዱት መካከልም የሥዕል ዐውደ ርዕይና የመጻሕፍት ምረቃ መርሃ ግብሮች ይገኙበታል፡፡ ለመረጃ ይሆንዎት ዘንድ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጥቂቶቹን እንደሚከተለው አዘጋጅቷቸዋል፡፡
መጻሕፍት
“ዮም” የተሰኘ በኦቲዝም ዙሪያ የሚያጠነጥንና በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሠረተ መጽሐፍ ተመርቆ ለንባብ በቅቷል፡፡ በደራሲ ንሴብሖ ፍቅሬ የተጻፈው ይህ መጽሐፍ፣ በኦቲዝም ጥላ ሥር ያሉ ልጆች የሚገጥሟቸውን ማኅበራዊ ጫናዎችና ቤተሰቦቻቸው የሚጋፈጡትን የሕይወት ፈተና ከራሳቸው ገጠመኝ በመነሳት የሚያሳይና በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ደራሲው የ11 ዓመት ዕድሜ ያለው “ዮም” የተባለ በኦቲዝም ጥላ ሥር ያለ ልጅ አባት ሲሆኑ፣ ልጃቸው የሕይወት ዘመን ክትትልና ድጋፍ የሚሻ በመሆኑ ሁኔታው በቤተሰቡ ላይ የፈጠረውን ጫና እና በአጠቃላይ መደረግ ስላለባቸው መፍትሔዎች ሐሳባቸውን አጋርተውበታል፡፡
በሌላ መረጃ “የተጋረደው ፈርጥ” መጽሐፍ ከነገ በስትያ ይመረቃል። መጽሐፉ የሙዚቀኛ ተሾመ ሲሳይን ሕይወትና ሥራዎች የሚዳስስ ሲሆን፣ የተጻፈውም በዳግማዊ አሰፋ ነው፡፡ መጽሐፉ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ ተመርቆ ለንባብ ይበቃል፡፡ የመጽሐፉ ገቢ ለመቄዶንያ ድጋፍ እንደሚውል የተነገረ ሲሆን፣ በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ አንጋፋና ወጣት አርቲስቶች፣ የሙዚቀኛው የሙያ አጋሮች፣ የጥበብ አድናቂዎች፣ ወዳጅ ዘመዶቹና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይገኛሉ ተብሏል፡፡
በተጨማሪም “ሃያ ሦስት” የተሰኘው የዳንኤል አብርሃ መጽሐፍ 2ኛ ዕትም ለንባብ በቅቷል፡፡ ደራሲው ከ11 ዓመታት በፊት በሊቢያ በአይ ኤስ አይ ኤስ (ISIS) የሽብር ቡድን ኢትዮጵያውያን ሲገደሉ ከሞት ባመለጠ ወጣት የተጻፈ ሲሆን፣ ስለ ስደት አስከፊነት የሚተርክና የሚያስተምር ነው፡፡
የሥዕል ዐውደ ርዕይ
“ዓድዋ” የተሰኘው የቡድን የሥዕል ዐውደ ርዕይ ከነገ በስትያ ይጠናቀቃል። በሥራው ላይ 7 ሰዓሊያን በጋራ ተሳትፈዋል፡፡ ሰዓሊያኑም አኑማ ኃይሉ፣ የሱቃል ተስፋዬ፣ ዮርዳኖስ ውቤ፣ እዮብ እሸቱ፣ ሱራፌል ከተማ፣ ዮዲት ወልደማርያም እና ዘካሪያስ ከተማ ናቸው፡፡ ዐውደ ርዕዩን ፈንድቃ የባህል ማዕከል እና ኃያት ረጀንሲ ሆቴል በመተባበር ያዘጋጁት ነው፡፡
የሥዕል ውድድር ለልጆች
የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ የዓለም የቲቢ ቀንን ምክንያት በማድረግ ልዩ የሕፃናት የሥዕል ውድድር አዘጋጅቷል፡፡ በውድድሩ
የሚሳተፉት ከ3ኛ እስከ 6ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች ሲሆኑ፣ የሥዕሉ መጠን ከA4 ወረቀት መጠን በላይ መሆን አለበት ብሏል፡፡ በእርሳስ፣ በቀለም ወይም በከለር
መሳል የሚቻል ሲሆን፣ ከሥዕሉ ጀርባ የተማሪው ሙሉ ስም፣ የትምህርት ቤቱ ስም እና የስልክ ቁጥር መጻፍ እንዳለበትም አሳውቋል፡፡ ውድድሩ የሚቆየው እስከ መጋቢት 11 ድረስ እንደሆነም ኮሌጁ ገልጿል፡፡
በጊዜው አማረ