በፈረንጆቹ የካቲት 17 ቀን 2026 በጀርመን መዲና በርሊን በተካሄደው የዘንድሮው 76ኛው ዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫል ላይ፣ የኢትዮጵያ ስም በክብርና በኩራት ጎልቶ ተደምጧል። የዓለም ሲኒማን መልክ ከቀየሩ ጥቂት የጥበብ ሰዎች መካከል አንዱ የሆነው ኢትዮጵያዊው ፕሮፌሰር ሃይሌ ገሪማ የመድረኩ የክብር እንግዳ ሆኖ ተሰይሟል። ኃይሌ የፌስቲቫሉ የላቀ የክብር ሽልማት የሆነውን የ‘በርሊናሌ ካሜራ’ ሽልማት ተረክቧል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በትልቅነቱ የሚጠቀሰው ይህ ሽልማት፣ ለዘመናት ለዘለቀ የኪነ-ጥበብ ተጋድሎ፣ ለማይበገረው የፈጠራ ጽናት እና ለዓለም ሲኒማ አዲስ ቀለም ለጨመሩ ባለሙያዎች የሚሰጥ ልዩ እውቅና ነው። ፕሮፌሰር ሃይሌ ይህን ክብር ሲቀበል፣ የራሱን የግል ስኬት ብቻ ሳይሆን፣ የአፍሪካን ሲኒማ ከፍታና ጥቁር ህዝቦች የራሳቸውን ታሪክ በራሳቸው አንደበት የመተረክ መብታቸውን በዓለም አደባባይ በድጋሚ ያስመሰከረበት ታሪካዊ አጋጣሚ ሆኗል።
ይህ ሽልማት ሃይሌ ገሪማ ላለፉት አምስት አስርት ዓመታት በፊልም ኢንዱስትሪው ውስጥ ለከፈለው መስዋዕትነት የተሰጠ ትልቅ ምላሽ ነው። ፕሮፌሰሩ በሆሊውድ የንግድ ቀመሮች ሳይወሰን፣ የጥቁር ህዝቦችን ታሪክ፣ ስቃይና ድል በራሳቸው የስነ ውበት እሳቤ ለመግለጽ ያሳየው ቆራጥነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ አክብሮትን አስገኝቶለታል። በፌስቲቫሉ ላይ የኢትዮጵያ አርበኞች ለነፃነታቸው የከፈሉትን መስዋዕትነት የሚዘክረው የፕሮፌሰሩ ፊልም መቅረቡ፣ ሽልማቱን ከግል እውቅና ባለፈ የታሪክና የማንነት ድል ያደርገዋል። ይህም ለወጣቶቹ የአፍሪካ ፊልም ባለሙያዎች ትልቅ መነሳሳትን የሚፈጥር ሲሆን፣ የራስን ታሪክ ለዓለም ለማሳየት የሌሎችን ፈቃድ መጠበቅ እንደሌለብንና በእውነት ላይ የተመሰረተ ጥበብ ዘላቂ ክብርን እንደሚያጎናጽፍ በተግባር ያሳየ ክስተት ነው። የአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍል በየካቲት ወር የሚከበረውን የአድዋ ድል በዓልና የጥቁር ህዝቦች ወር መነሻ በማድረግ የሃይሌ ገሪማ ኪነ ጥበባዊ አበርክቶ፣ የኢትዮጵያ አርበኞች ተጋድሎ በኪነ ጥበብ መድረክና ስለፊልሞቹ ምንነት በጨረፍታ ልናስቃኛችሁ ወድደናል፡፡
ዓድዋ- የጥቁር ህዝብ የነፃነት ቃል ኪዳን
የዓድዋ ድል በታሪክ ምሁራን ዘንድ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ህዝብ የነፃነት ፋና ተደርጎ ይወሰዳል። የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ራይሞንድ ጆናስ በፈረንጆቹ 2011 ለንባብ ባበቁት ‘The Battle of Adwa፦ African Victory in the Age of Empire’ መጽሐፋቸው ላይ፣ “ዓድዋ የአውሮፓ የበላይነት በአፍሪካ ምድር ያከተመበትና የዘመናዊት አፍሪካ ሉዓላዊነት መሰረተ-ድንጋይ የተጣለበት ታላቅ ክስተት ነው። ይህ ድል ‘ጥቁር ህዝብ የበታች ነው’ የሚለውን የቅኝ ገዢዎች ስሁት ትርክት በመስበር፣ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ጥቁሮች ቀና ብለው እንዲሄዱና ለሰብአዊ መብታቸው እንዲታገሉ የስነ-ልቦና ስንቅ ሆኗቸዋል።” ሲሉ አስፍረዋል፡፡
ይህ የዓድዋ ድል የፈጠረው ስነ-ልቦናዊ መነቃቃት በአሜሪካ የጥቁሮች የጥበብና የማንነት ንቅናቄ በሆነው “የሃርለም ህዳሴ” ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ ነበረው። በወቅቱ የነበሩ እንደ ዊሊያም ዱቦይስ ያሉ የፓን-አፍሪካኒዝም አባቶችና ባለቅኔዎች፣ የዓድዋን ድል ከጥቁር ህዝቦች የመብት ጥያቄ ጋር በማስተሳሰር በግጥሞቻቸውና በሙዚቃዎቻቸው አንጸባርቀውታል። ይህም ዓድዋ የሃርለምን ንቅናቄ፣ የሃርለም ንቅናቄ ደግሞ የፓን-አፍሪካኒዝም እሳቤን እንዲወልዱ በማድረግ ረገድ የሰንሰለቱ መጀመሪያ መሆኑን ያሳያል።
የሲኒማ ሊቁ ፕሮፌሰር ሃይሌ ገሪማ፣ የዓድዋ ድልንና ድሉ ለጥቁር ህዝቦች ያለውን ጥልቅ ተምሳሌትነት ለፈጠራ ስራዎቹ ዋነኛ ግብዓት በማድረግ ረገድ ቀዳሚው ምሁርና ከያኒ ነው። ሃይሌ ዓድዋን እንደ አንድ ተራ የታሪክ ክስተት ወይም ያለፈ የጦርነት ድል ብቻ አይመለከተውም። ይልቁንም የጥቁር ህዝቦች እንደገና መነሳት (African Renaissance) እና የነፃነት መንፈስ ዳግም መወለድ ተምሳሌት መሆኑን በፊልም ስራዎቹ ላይ በጉልህ አሳይቷል። ለፕሮፌሰር ኃይሌ ዓድዋ ማለት አፍሪካውያን በቅኝ ግዛት ስር የወደቀውን ማንነታቸውንና የተሰበረውን ስነ-ልቦናቸውን ቀና ያደረጉበት፣ “አልሸነፍም” ባይነታቸውን ለዓለም ያስመሰከሩበት የክብር ማህተም ነው። ይህንኑ እውነት በምስልና በድምፅ በመቅረጽ፣ ድሉ ከኢትዮጵያ ድንበር አልፎ በመላው ዓለም ለሚገኙ ጥቁር ህዝቦች የኩራት ምንጭ እንዲሆን በላቀ የሲኒማ ጥበብ ማሳየት ችሏል።

ለዚህ ጥሩ ማሳያ በፈረንጆቹ 1999 ለዕይታ የበቃው ‘ዓድዋ፡ የአፍሪካ ድል’ (Adwa: An African Victory) የተሰኘው ዝነኛ ዘጋቢ ፊልም ነው። ከሰሞኑ ደግሞ የዚህ ፊልም ሁለተኛ ክፍል የሆነውና የኢትዮጵያ አርበኞች በሁለተኛው የጣሊያን ወረራ (ከ1928 እስከ 1933 ዓ.ም) ያደረጉትን ተጋድሎ የሚዘክረው “Black Lions – Roman Wolves” (ጥቁር አንበሶች – የሮማ ተኩላዎች) የተሰኘው ፊልም ሌላኛው ማሳያ ነው፡፡
በተለይ የሃይሌን የታሪክ ተመራማሪነት፣ የጥበብ ሰውነትና ታላቅ አሰላሳይነቱን በጉልህ የሚያሳየው ‘ዓድዋ፡ የአፍሪካ ድል’ (Adwa: An African Victory) የተሰኘው ዝነኛ ዘጋቢ ፊልሙ ነው። ይህ ፊልም ተራ የጦርነት ትረካ ሳይሆን፣ የአንድን ህዝብ ህያው ነፍስና ለማንነቱ የከፈለውን ዋጋ በምስልና በድምፅ የቀረጸ የታሪክ ሰነድ ነው።
ሃይሌ ‘ዓድዋ’ን ሲሰራ የተጠቀመበት ስልት የታሪክ አጻጻፍን የተለመደ አካሄድ የቀየረ ነው። ታሪክ አብዛኛውን ጊዜ በነገስታትና በባለስልጣናት ዙሪያ ብቻ ሲሽከረከር ቢታይም፣ ፕሮፌሰር ሃይሌ ግን የታሪኩ ቀጥተኛ ባለቤት የሆኑትን የዘመኑን አዛውንቶችና የአርበኞች ልጆችን ምስክርነት በስፋት ተጠቅሟል። በዚህም ታሪክ ከቤተ-መንግስት ሰነዶች ወጥቶ በህዝብ አንደበት፣ በቤት ውስጥ ጨዋታና በቃል ግጥሞች እንዲነገር በማድረግ፣ የታሪኩን ባለቤትነት ወደ ተራው ህዝብ መልሶታል። ይህም ፊልሙን እውነተኛ፣ ስሜት የሚነካና በሰነድ የተደገፈ ጠንካራ ስራ ያደርገዋል።
ይህ ፊልም ከዓድዋ ድል በስተጀርባ ያለውን አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ትርጉም በግልጽ ያስቀምጣል። ዓድዋ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን፣ በመላው አፍሪካና በዲያስፖራ ለሚገኙ ጥቁር ህዝቦች የነፃነት፣ የክብርና የድል ተምሳሌት መሆኑን ሃይሌ በስራዎቹ ይሞግታል። በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር ለነበሩ ህዝቦች ሁሉ፣ “ጥቁር ህዝብ ነጭን ወራሪ ማሸነፍ ይችላል” የሚል ተስፋ የሰነቀ የታሪክ ምዕራፍ መሆኑን በማሳየት፣ የዓድዋን ድል የዓለም ጥቁር ህዝቦች የጋራ ቅርስ አድርጎታል፡፡
የበርሊኑ ምሽትና የአርበኞች ዝክር
በ76ኛው የበርሊን ዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫል መድረክ ላይ፣ የፕሮፌሰር ሃይሌ ገሪማ የክብር ሽልማት ሥነ-ሥርዓት በከፍተኛ ድምቀት የታጀበ ነበር። በዕለቱ በታዋቂው የፊልም አዳራሽ ውስጥ የተሰበሰቡት የዓለም ሲኒማ ባለሙያዎች፣ ሃያሲዎችና የጥበብ አፍቃሪዎች ለኢትዮጵያዊው የሲኒማ ባለውለታ አክብሮታቸውን ሲቸሩ የታየበት ትዕይንት፣ የሃይሌን የዓመታት ድካምና ተፅዕኖ በግልጽ ያሳየ ነበር። በዚህ ልዩ ምሽት ላይ፣ በሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ወቅት የኢትዮጵያውያን አርበኞችን ተጋድሎና ጽናት የሚዘክረው “ጥቁር አንበሶች – የሮማ ተኩላዎች” አዲሱ የሃይሌ ገሪማ ፊልም ለዕይታ የቀረበ ሲሆን፣ በታሪካዊው እውነታና በፊልሙ ጥበብ የታደመው ተመልካች በዝምታና በግርምት ሲከታተል ውሏል።
ይህ በፌስቲቫሉ ላይ ትኩረት የሳበው ፊልም፣ ኢትዮጵያውያን ወራሪውን የጣሊያን ጦር በገዛ አገራቸው ምድር ላይ እንዴት በጀግንነት እንደመከቱት የሚያሳይ ጥልቅ ስራ ነው። ፊልሙ ከቀደሙት የሃይሌ ስራዎች ጋር በተቆራኘ መልኩ፣ የኢትዮጵያን አርበኞች እንደ ተራ ተዋጊዎች ሳይሆን፣ ለክብራቸውና ለማንነታቸው የሚጋደሉ፣ የራሳቸው ፍልስፍና ያላቸው ባለታሪኮች አድርጎ ስሏቸዋል። በዕለቱ የነበረው ሁኔታም ፊልሙን ከመመልከት ባለፈ፣ በወቅቱ የነበረውን ግፍና የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ጥማት በውይይት መድረኮች ላይ ጭምር እንዲነሳ አድርጓል። ፕሮፌሰር ሃይሌም በዚሁ መድረክ በሰጠው ማብራሪያ፣ “ታሪክ የሚዘከረው ለማልቀስ ሳይሆን፣ ለቀጣዩ ትውልድ ስነ-ልቦናዊ ጥንካሬን ለመስጠት ነው” በማለት የፊልሙን ትልቅ ዓላማ አስረድቷል።
በዕለቱ በበርሊን አደባባይ የታየው የክብር ስነ-ስርዓት፣ ሃይሌ ገሪማ በዓለም ሲኒማ ውስጥ ያለውን የማይናወጥ ቦታ ያረጋገጠ ነበር። ሽልማቱን በተቀበለበት ወቅት ያደረገው ንግግር የብዙዎችን ቀልብ የሳበ ሲሆን፣ ጥቁር ህዝቦች የራሳቸውን ታሪክ በራሳቸው መንገድ የመተረክ አስፈላጊነት ላይ በድጋሚ ትኩረት ሰጥቷል። በፌስቲቫሉ የታደሙ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችም፣ ሃይሌ በፊልሞቹ ውስጥ የሚጠቀማቸው “የጥቁር ሲኒማ ቋንቋ” (Black Cinematic Language) ምን ያህል ተፅዕኖ ፈጣሪ እንደሆኑና የኢትዮጵያውያን አርበኞች ታሪክ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊታወቅ የሚገባው የሰብዓዊ መብት ትግል ምሳሌ መሆኑን በሰፊው ዘግበውታል።
የበርሊን ዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫል ዳይሬክተር ትሪሺያ ቱትል እንደገለጹት፣ የዘንድሮው የ‘በርሊናሌ ካሜራ’ ሽልማት ለሃይሌ ገሪማ የተሰጠው ዓለም ስለሚረዳበት መንገድ አዲስ እይታን ለፈጠሩና በጭቆና፣ በተቃውሞ እንዲሁም በዲኮሎናይዜሽን (ከቅኝ አገዛዝ አስተሳሰብ መላቀቅ) ዙሪያ ላበረከቷቸው ስራዎች እውቅና ለመስጠት ነው። ፌስቲቫሉ ከሃይሌ ጋር የቆየ ቁርኝት ያለው ሲሆን፣ በተለይም እ.ኤ.አ በ1993 ‘ሳንኮፋ’ በተሰኘው ስራቸው በውድድር መድረክ ከቀረቡበት ጊዜ ጀምሮ ለጥቁር ሲኒማ ባላቸው ቁርጠኝነት እንደሚደነቁ ገልጸዋል።
በዘንድሮው 76ኛው ፌስቲቫል ላይ ልዩ ትኩረት ያገኘውን የሃይሌ ገሪማ አዲሱ ፊልም ለዘጠኝ ሰዓታት ያህል የሚዘልቅ ግዙፍ ስራ ነው፡፡ ፊልሙን ለመስራት ከሰላሳ ዓመታት በላይ ፈጅቷል፡፡ ይህ ታላቅ ፊልም የጣሊያንን ቅኝ አገዛዝ ታሪክና አፈ ታሪክ በጥልቀት የሚመረምር እንዲሁም ለኢትዮጵያ አርበኞች ተጋድሎ መታሰቢያነት የቀረበ ሲኒማዊ ሰነድ መሆኑ የ‘በርሊናሌ ካሜራ’ ሽልማት ባሰራጨው መግለጫ ላይ አስፍሯል፡፡
በአጠቃላይ፣ ፕሮፌሰር ሃይሌ ገሪማ በበርሊን የፊልም ፌስቲቫል ያገኘው እውቅና፣ ከዓድዋ ድል የጀመረውና በሃርለም ህዳሴ ያለፈው የጥቁር ህዝቦች የነፃነትና የማንነት ትግል በሲኒማው መድረክ ያገኘው ትልቅ ድል ነው። ሃይሌ በኪነ ጥበባዊ ሥራዎቹ በኩል ፓን-አፍሪካኒዝምን በተግባር በመኖር፣ አፍሪካውያን ህመማቸውን አውቀውና ራሳቸውን ወደው ለዓለም አዲስ የሰላምና የእኩልነት ሃሳብ እንዲያዋጡ መንገድ ጠራጊ ሆኗል። በዚህም ፕሮፌሰር ሃይሌ ገሪማ በ76ኛው የበርሊን ዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫል ላይ የ‘በርሊናሌ ካሜራ’ የክብር ሽልማት ማሸነፉ፣ የግማሽ ክፍለ ዘመን ጥበባዊ ተጋድሎው ፍሬ ማፍራቱን የሚያሳይ ታሪካዊ ክስተት ነው።
በአብርሃም ገብሬ