ልጆች፤ ስለኔልሰን ማንዴላ መታሰቢያ ሙዚየም ምን ያህል ታውቃላችሁ?

You are currently viewing ልጆች፤ ስለኔልሰን ማንዴላ መታሰቢያ ሙዚየም ምን ያህል ታውቃላችሁ?

ልጆች፤ የየካቲት ወር የጥቁሮች ታሪክ ወር ተብሎ ይከበራል፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ለጥቁር ሕዝቦች መብትና ነጻነት የታገሉ ታላላቅ ሰዎችንና ታሪካዊ ክስተቶችን ለማስታወስ ነው፡፡ እኛም በዚህ ረገድ በግንባር ቀደምነት ከሚጠቀሱት መካከል ስለሆኑት፣ ለኢትዮጵያ ልዩ ፍቅር ስለነበራቸው፣ በስማቸውም መታሰቢያ ሙዚየም ስለተከፈተላቸው አንድ ሰው ልናስተዋውቃችሁ ወደድን፡፡

እኒህ ሰው እውቁ የነጻነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ ናቸው፡፡ የተወለዱት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ሐምሌ 18 ቀን 1918 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ማቬዞ  ነው። በወቅቱ በደቡብ አፍሪካ የነበረውን ዘረኛና ጨቋኝ የአፓርታይድ ሥርዓት በቃ ለማለት በብርቱ ታግለዋል፡፡ ለዚህ ህልማቸው አቅም የሚሆን ወታደራዊ ስልጠናና ስልታዊ ዕውቀት ፍለጋም ወደ ኢትዮጵያ እንደመጡ መረጃዎች ያመላክታሉ።

በወቅቱ ኔልሰን ማንዴላ የኢትዮጵያ ፓስፖርት ተዘጋጅቶላቸው በአዲስ አበባ ኮልፌ የፌደራል ፖሊስ ፈጥኖ ደራሽ ማዕከል ውስጥ ለጥቂት ወራት  ወታደራዊ ስልጠና ወስደዋል። ዛሬ ያ ታሪካዊ ቦታ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በኋላ በዘመናዊ መልክ ታድሶና ተገንብቶ ወደ ሙዚየምነት ተቀይሯል። ሙዚየሙ የነጻነት ታጋዩን የኔልሰን ማንዴላን ገድል ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ የነጻነት ትግል ያበረከተችውን የማይተካ ሚና ለዓለም የሚያሳይ ትልቅ የታሪክ ማህደር ሆኖ ያገለግላል።

ልጆች፤ ማንዴላ በቆዳ ቀለም ሳይሆን የሁሉም ዜጋ ሰብአዊ መብቶች የሚከበሩባት፤ እኩል እድል የሚሰጥባት ደቡብ አፍሪካን ለመፍጠር ሲያደርጉ የነበረው የነጻነት ትግል ያለምንም ፈተና የተከናወነ አይደለም፡፡ ለ27 ዓመት እስር ቤት እንዲቆዩ አድርጓቸዋል።

ልጆች፤ ኔልሰን ማንዴላ ከእስር እንደተፈቱ ከጎበኟቸው ሀገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ነበረች። ምክንያታቸውን ‘ረጅሙ የነጻነት ትግል ጉዞ’ በተሰኘው መጽሐፋቸው “ኢትዮጵያ በኔ ውስጥ ልዩ ስፍራ አላት። በፈረንሳይ፣ በእንግሊዝ እና በአሜሪካ ያደረኳቸው ጉብኝቶች ቢደመሩ እንኳን በኢትዮጵያ ከነበረኝ ቆይታ አይበልጡም።” በማለት ያላቸውን ልዩ ስሜት ገልጸዋል።

ስለዓድዋ ድልም “በዓድዋ ላይ የተገኘው ድል በውጊያ የተገኘ ድል ብቻ አይደለም። ይልቁንም መንፈሳዊ ድል ጭምር እንጂ። ዓድዋ የአፍሪካ ተስፋ ትዕምርት (ምልክት) ነው፡፡ የአፍሪካዊነት የዘር ሃረግ ግንዴ የተተከለባት ሀገር ትመስለኛለች” ብለዋል፡፡ ኔልሰን ማንዴላ ለኢትዮጵያ ያላቸው ፍቅርና ክብር በጣም ጥልቅ ነበር። ኢትዮጵያን እንደ ሁለተኛ ሀገራቸው፣ አዲስ አበባን ደግሞ የነፃነት ትግላቸው መነሻ አድርገው ይቆጥሯት ነበር።

ለእኒህ የነጻነት ታጋይ ከሙዚየሙ ባለፈ በአፍሪካ ህብረት ዋና መስሪያ ቤት የአፍሪካ መሪዎች የሚሰበሰቡበት ትልቅ አዳራሽም በስማቸው ተሰይሞላቸዋል፡፡

ኔልሰን ማንዴላ ለነፃነት ባደረጉት ትግል እንደአውሮፓውያን አቆጣጠር በ1993 የሠላም ኖቤል ሽልማት ማግኘት መቻላቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ።

በፋንታነሽ ተፈራ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review