አርሰናል ፣ ማንችስተር ሲቲ እና ቼልሲ የኤፍ ኤ ካፕ 5ኛ ዙር ጨዋታቸውን ዛሬ ያደርጋሉ

You are currently viewing አርሰናል ፣ ማንችስተር ሲቲ እና ቼልሲ የኤፍ ኤ ካፕ 5ኛ ዙር ጨዋታቸውን ዛሬ ያደርጋሉ

AMN- የካቲት 28/2018 ዓ.ም

የኤፍ ኤ ካፕ 5ኛ ዙር ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥሎ ሲደረጉ ሦስት ግጥሚያዎች ይጠበቃሉ።

የፕሪምየር ሊጉ መሪ አርሰናል ከሜዳው ውጪ በሊግ 1 የሚወዳደረው እና በመሀላቸው የ59 ደረጃ ልዩነት ያለው ማንስፊልድ ታውንን ይገጥማል።

የ14 ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ አርሰናል ጨዋታውን ካሸነፈ ከስድስት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሩብ ፍፃሜውን ይቀላቀላል።

በጨዋታው በአርሰናል በኩል የቁርጭምጭሚት ጉዳት የገጠመው ዊሊያም ሳሊባ ይሳተፋል ተብሎ አይጠበቅም።

በማንስፊልድ ሜዳ ፊልድ ሚል የሚደረገው ጨዋታ 9:15 ሲል ይጀምራል።

በሌላ ጨዋታ ኒውካስትል ዩናይትድ በሴንት ጀምስ ፓርክ ማንችስተር ሲቲን ምሽት 5 ሰዓት ያስተናግዳል።

ባለፈው ዓመት በክሪስታል ፓላስ ተሸንፎ ዋንጫ ያጣው ማንችስተር ሲቲ ዛሬ ምሽት ከኒውካስትል ከባድ ፈተና ይጠብቀዋል።

በቀጣይ ሳምንት አጋማሽ ከሪያል ማድሪድ ጋር የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ ያለበት ፔፕ ጋርዲዮላ በመርሐግብሩ መደራረብ ደስተኛ አይደለም።

ከቀናት በፊት በፕሪሚየር ሊጉ ከኖቲንግሃም ፎረስት ጋር አቻ ተለያይቶ ነጥብ የጣለው ሲቲ በሁሉም ውድድሮች ውስጥ ይገኛል።

ፔፕ ጋርዲዮላ ከዛሬ ጨዋታ በፊት በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ በመርሐግብሩ መጣበብ ደስተኛ ባይሆንም ኤፍ ኤ ካፕ ትልቅ ትኩረት የሚሰጡት ውድድር እንደሆነ ተናግሯል።

ምሽት 2:45 ላይ ቼልሲ የቻምፒየንሺፕ ተወዳዳሪው ሬክሳምን የሚገጥምበት ጨዋታም ዛሬ ይጠበቃል።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review