በፅንስ እድገት ወቅት የሚከሰቱ የአካል ጉድለቶች፤ መንስኤዎችና መከላከያ መንገዶች

You are currently viewing በፅንስ እድገት ወቅት የሚከሰቱ የአካል ጉድለቶች፤ መንስኤዎችና መከላከያ መንገዶች
  • Post category:ጤና

AMN- የካቲት 28/2018 ዓ.ም

በፅንስ እድገት ወቅት የሚፈጠሩ የአካል ክፍል አፈጣጠር ችግሮች በህፃናት ጤና ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ከሚያሳድሩ ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳሉ።

በተለይም ከጭንቅላት፣ ከአንጎል እና ከህብለ-ሰረሰር ጋር የተያያዙ እክሎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መጥተዋል።

እነዚህ ችግሮች በጊዜያቸው ካልተለዩ በህፃኑ የረጅም ጊዜ ጤና፣ እድገት እና የመማር ብቃት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ።

በፅንስ አፈጣጠር ችግሮች ላይ የሚሰሩት ስፔሻሊስት ሀኪም ዶ/ር ብርሃኑ ከበደ ለኤ ኤም ኤን እንደገለጹት፤ ለእነዚህ የአካል ጉድለቶች መከሰት ከሚጠቀሱ ዋነኛ መንስኤዎች መካከል የፎሊክ አሲድ እጥረት ቀዳሚ ስፍራ ይይዛል።

ፎሊክ አሲድ በፅንስ እድገት ወቅት ለአንጎልና ለህብለ-ሰረሰር ትክክለኛ እድገት አስፈላጊ ንጥረ ነገር መሆኑንም ገልጸዋል።

በተጨማሪም የደም ስኳር መጠናቸውን ያልተቆጣጠሩ፣ የሚጥል በሽታ መድኃኒቶችን የሚወስዱ እና ለከፍተኛ ጨረር የሚጋለጡ እናቶች ከእነዚህ ችግሮች ጋር የተያያዙ የአደጋ ሁኔታዎችን እንደሚያስተናግዱ ዶ/ር ብርሃኑ ጠቁመዋል።

ቀደም ሲል ተመሳሳይ ችግር ያለበት ልጅ የወለዱ እናቶች ውስጥ የቤተሰብ ታሪክ ከነበረ ከመንስኤዎቹ መካከል ተጠቃሽ ሊሆን እንደሚችልም ገልጸዋል።

ዶ/ር ብርሃኑ እንደሚሉት፣ የአካል አፈጣጠር ችግሮችን ቀድሞ ለመለየት ዘመናዊ የህክምና ምርመራዎች ከፍተኛ ሚና አላቸው።

በተለይም ፅንሱ በ13ኛው ሳምንት ላይ እያለ የሚደረገው የአልትራሳውንድ ምርመራ አብዛኞቹን የአካል ጉድለቶች ቀድሞ ለመለየት እንደሚረዳ ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የላቦራቶሪ ምርመራዎችን በመጠቀም ከእናት፣ ከአባት ወይም ከፅንሱ የደም ናሙና በመውሰድ የዘር ውርስ (Genetic) መንስኤዎችን ለማወቅ የሚያግዙ ጥልቅ ምርመራዎች እንደሚካሄዱም ጠቁመዋል።

በህክምና ቴክኖሎጂ እድገት ምክንያት አንዳንድ የፅንስ አፈጣጠር ችግሮችን ፅንሱ ሳይወለድ በማህፀን ውስጥ እያለ ህክምና መስጠት መጀመሩንም ዶ/ር ብርሃኑ ገልጸዋል።

በጭንቅላት ውስጥ የሚጠራቀም ፈሳሽን የፈሳሽ ማስወገጃ ቱቦ በመጠቀም ወደ ሆድ እንዲፈስ በማድረግ የጭንቅላት እብጠትን መቀነስ እንደሚቻልም አብራርተዋል።

በተመሳሳይም ክፍተት ያለባቸውን የህብለ-ሰረሰር ክፍሎች ፅንሱ ሳይወለድ በማህፀን ውስጥ በቀዶ ጥገና መዝጋት እንደሚቻል ገልጸዋል።

ከወሊድ በኋላም ህፃኑ በጤና ባለሙያዎች በቅርብ ክትትል እንዲጠበቅ ይመከራል፤ በተለይም የአንጎል እድገቱን እና የመማር ብቃቱን ለማሻሻል ቀጣይነት ያለው ክትትል አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል።

እናቶች ከመፀነሳቸው በፊትም ሆነ በእርግዝና ወቅት በፎሊክ አሲድ የበለፀጉ ምግቦችን መመገብ እና የፎሊክ አሲድ እንክብሎችን መውሰድ፣ የህፃናት የአካል ጉድለቶች መከሰትን በከፍተኛ መጠን ሊቀንስ እንደሚችል ዶ/ር ብርሃኑ ገልጸዋል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review