“ዓድዋ የኢትዮጵያውያን ዘመን ተሻጋሪ ድል እና የወል ትውስታ” በሚል ርዕስ የተዘጋጀውን የታሪክ መጽሐፍ ተመረቀ

You are currently viewing “ዓድዋ የኢትዮጵያውያን ዘመን ተሻጋሪ ድል እና የወል ትውስታ” በሚል ርዕስ የተዘጋጀውን የታሪክ መጽሐፍ ተመረቀ

AMN – የካቲት 28/2018 ዓ.ም.

“ዓድዋ የኢትዮጵያውያን ዘመን ተሻጋሪ ድል እና የወል ትውስታ” በሚል ርዕስ የተዘጋጀውን የታሪክ መጽሐፍ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ፣ ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ተመርቋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው እንዳሠፈሩት ታሪክን ማወቅ ካለፈው ዘመን ጋር መነጋገር፥ ከስህተት ተምሮና በጎውን አጉልቶ ወደተሻለ ብርሃን መሻገር ማለት ነው ብለዋል።

ዛሬ ያስመረቅነው መጽሐፍም የዓድዋን ድል ከእኛ ከኢትዮጵያውያን አንጻር በመዘከር፣ የአንድነት ድላችን መሆኑን በማውሳት ለወደፊት ጉዟችን ስንቅ የሚሆኑ በርካታ ቁም ነገሮችን ይዞ ቀርቧል በማለት ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም በተለያዩ የይዘት ሥራዎች ተበታትኖ የነበረውን አኩሪ ታሪክ፣ በተደራጀና በተሟላ መልኩ በመጽሐፍ ሰንደን ለትውልዱ “እነሆ” ብለዋል።

ዓድዋንና መሰል የጋራ ድሎቻችንን የሚዘክሩ እንዲህ ያሉ አሰባሳቢ የታሪክ ሥራዎች ይበልጥ ሊበረታቱ ይገባል፤ ይህም ትውልዱ የተከፈለለትን ክቡር ዋጋ እንዲገነዘብ እና የራሱን አኩሪ ታሪክ እንዲሠራ የሚያነሳሳ ይሆናል ብለዋል።

ከንቲባዋ እንደገለጹት ከ128 ዓመታት በኋላ የገነባነው የዓድዋ ድል መታሰቢያ “ቋሚ ሙዚየም” ሲሆን፤ ይህ ዛሬ ያስመረቅነው መጽሐፍ ደግሞ ሁሉም ቦታ መድረስ የሚችል “ተንቀሳቃሽ ሙዚየም” ሆኖ ያገለግላል።

መጽሐፉን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ ወደፊት በተለያዩ ቋንቋዎች ተዘጋጅቶ እንደሚታተምና የመጽሐፉ ሽያጭ ገቢም የዓድዋ ድል መታሰቢያን ይበልጥ ለማደራጀትና ለማላቅ እንደሚውል አስታውቀዋል።

የመጽሐፉን ደራሲ ዶክተር አሻግሬ ገብረወልድን እና በሥራው ላይ አስተያየት ከመስጠት አንስቶ የየራሳቸውን አበርክቶ ያዋጡትን በሙሉ “እንኳን ደስ አላችሁ” ብለው የዚህ አኩሪ የጀግንነት ታሪክ ባለቤት የሆኑ መላው ኢትዮጵያውያን፣ በተለይም ወጣቶች፣ መጽሐፉን እንዲያነቡት፣ እንዲወያዩበትና እንዲመራመሩበት ከንቲባዋ ጋብዘዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review