AMN – የካቲት 28/2018 ዓ.ም.
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አማካይነት የቀረበው “ምርጫዬ” የተሰኘው የምርጫ መመዝገቢያ ቴክኖሎጂ በቀላሉ የምርጫ ምዝገባ ለማካሄድ እንደረዳቸው ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በይፋ የተጀመረውን የመራጮች ምዝገባ ሒደት በተወሰኑ የምርጫ ጣቢያዎች ተገኝቶ ምልከታ አድርጓል፡፡
በዚሁ መሠረት በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በተዋወቀው “ምርጫዬ” የምርጫ መተግበሪያን ዜጎች በእጅ ስልካቸው ላይ በመጫን ምዝገባ ሲያከናውኑ አግኝተናቸዋል፡፡
ተመዝጋቢዎቹ እንደገለጹት መተግበሪያው የመራጮችን ጊዜ የቆጠበ እና ምቹ ሁኔታንም የፈጠረ መሆኑን ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በዛሬው ዕለት ባስጀመረው የመራጮች ምዝገባ የመጀመሪያ ቀን ላይ ተመዝጋቢዎች በተለያዩ አመራጮች ነው ምዝገባቸውን እያካሔዱ የሚገኙት።
በተለይ ሰዎች በቀላሉ እና በእጅ ስልካቸው በመጠቀም የምዝገባ ሒደቱን የሚያከናውኑበት አማራጭ መቅረቡ ዕድሜያቸው ለምርጫ የደረሱ ዜጎች ሁሉ ምዝገባቸውን በቀላሉ ለማከናወን ዕድሉን እንዲጠቀሙበት ምዝገባ ሲከውኑ ያገኘናቸው ዜጎች ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
ምርጫው የሀገርን መጻዒ ዕጣ ፈንታ የሚወስን፥ ዜጎች ሕገመንግስታዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን የሚጠቀሙበት ጊዜ በመሆኑ ማኛውም ዕድሜው ለምርጫ የደረሰ ዜጋ ሁሉ ይህንን መብቱን በአግባቡ ሊጠቀምበት እንደሚገባም አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል፡፡
በስልክ በቀረበው አማራጭ ቴክኖሎጂ በመታገዝ የሚደረገው ምዝገባ ከዛሬ ጀምሮ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡
በሀብታሙ ሙለታ