AMN- የካቲት 29/2018 ዓ.ም
አበበች ጎበና ከኢትዮጵያ አልፎ ተርፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሰብአዊ መብትና በበጎ አድራጎት ሥራቸው የሚታወቁ ታላቅ ሴት ናቸው።
ብዙዎች “የአፍሪካዋ ማዘር ቴሬዛ” በሚል ስም ይጠሯቸዋል።
አበበች ጎበና የተወለዱት በሰሜን ሸዋ (ሰላሌ) ልዩ ስሙ አባያ በተባለ ቦታ ነው። በልጅነታቸው ቤተሰቦቻቸው ለትዳር ቢድሯቸውም፣ ያንን ሕይወት አልቀበልም በማለት ወደ አዲስ አበባ መጥተው በተለያዩ ሥራዎች በመሰማራት ሲተዳደሩ ቆይተዋል፡፡
የአበበች ጎበና የሕይወት አቅጣጫ የተቀየረው በ1973 ዓ.ም. በኢትዮጵያ በተከሰተው አስከፊ ድርቅ ወቅት እንደነበር የህይወት ታሪካቸዉ ያስረዳል፡፡
በግላቸው የጀመሩት ይህ ሥራ እያደገ ሄዶ አበበች ጎበና የሕፃናት እንክብካቤና ልማት ማኅበር የተባለውን ድርጅት እስከማቋቋም ደርሰዋል፡፡
አበበች ጎበና ለሥራቸው ላሳዩት ቅንነትና መስዋዕትነት ከሀገር ውስጥና ከዓለም አቀፍ ተቋማት በርካታ ሽልማቶችን ያገኙ ሲሆን ከነዚህ መካከል ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት እንዲሁም በተለያዩ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ዕውቅና ተችሯቸዋል፡፡
አበበች ጎበና “እኔ እናት ነኝ፤ እናት ደግሞ ልጆቿ ሲራቡ ማየት አትችልም” በሚለዉ ንግግራቸዉ ይታወሳሉ፡፡
አበበች ጎበና ሰኔ 27 ቀን 2013 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ቢለዩም የጀመሩት ድርጅት ግን ዛሬም ድረስ በሺዎች ለሚቆጠሩ ሕፃናት ተስፋ መሆኑን ቀጥሏል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም እኝህ ልበ ቀናና ደግ እናት ላበረከቱት የላቀ አስተዋጽኦ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ በየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የአበበች ጎበና እናቶችና ህፃናት ህክምና ማዕከልን በስማቸዉ ሰይሟል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ