የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች

You are currently viewing የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች

AMN – መጋቢት 1/2018 ዓ.ም

በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ 16 ክለቦች የሚሳተፉበት የጥሎ ማለፍ ዙር ጨዋታዎች ዛሬ ይጀምራሉ።

በጥሎ ማለፉ የመጀመሪያ ዙር ዛሬ አራት ጨዋታዎች ሲከናወኑ ባርሴሎና በሴንት ጀምስ ፓርክ ኒውካስትል ዩናይትድን ምሽት 5 ሰዓት የሚገጥምበት በጉጉት ይጠበቃል።

ሁለቱ ክለቦች በመስከረም ወር በውድድሩ የሊግ ምዕራፍ ላይ ተገናኝተው የስፔኑ ክለብ በማርከስ ራሽፎርድ ግቦች 2ለ1 ማሸነፉ ይታወሳል።

ዋንጫውን የማሸነፍ አቅም እንዳላቸው ከተመሰከረላቸው ክለቦች አንዱ የሆነው ባርሰሎና ከእንግሊዝ ክለቦች ጋር ያለው የእርስ በእርስ ግንኙነት የሚያኩራራ ነው።

የሀንሲ ፍሊኩ ቡድን ከእንግሊዝ ክለቦች ጋር ያደረጋቸውን አምስት የመጨረሻ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች አሸንፎ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፏል።

ኒውካስትል ዩናይትድ ባለፉት ተከታታይ አምስት የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታዎች ሽንፈት አልገጠመውም። ይህም በውድድሩ በታሪኩ ያለሽንፈት ብዙ ርቀት የተጓዘበት ሆኖ ተመዝግቦለታል።

ኒውካስትል ከባርሰሎና ጋር ሲጫወት የዛሬ ምሽቱ ለስድስተኛ ጊዜ ነው። ከዚህ ቀደም በነበራቸው አምስት ግንኙነት ኒውካስትል አንዱን ብቻ አሸንፏል ፤ ባርሰሎና አራቱን ጨዋታዎች በበላይነት አጠናቋል።

በሌሎች ጨዋታዎች የቡንደስሊጋው ሃያል ክለብ ባየርን ሙኒክ ወደ ቤርጋሞ አቅንቶ የጣልያኑን ክለብ አታላንታን ይገጥማል።

አትሌቲኮ ማድሪድ በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ላለመውረድ የሚጫወተው ቶተንሃም ሆትስፐርስን በዋንዳ ሜትሮፖሊታኖ የሚያስተናግድበት ጨዋታም ይጠበቃል። ጨዋታዎቹ ምሽት 5 ሰዓት ሲል የሚጀምሩ ይሆናል።

ምሽት 2:45 ላይ ጋላታሳራይ ከ ሊቨርፑል በራምስ ፓርክ ይጫወታሉ። ሁለቱ ቡድኖች በዚሁ ሜዳ በሊግ ምዕራፍ ተገናኝተው ጋላታሳራይ 1ለ0 ማሸነፍ ችሎ ነበር።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review