አለርት ሆስፒታል የአፍሪካ የፕላስቲክ ቀዶ ህክምና ባለሙያዎች መፍለቂያ እየሆነ ነው

You are currently viewing አለርት ሆስፒታል የአፍሪካ የፕላስቲክ ቀዶ ህክምና ባለሙያዎች መፍለቂያ እየሆነ ነው

AMN – መጋቢት 01/2018 ዓ.ም

የአለርት ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በኢትዮጵያ ብቸኛ የሆነውን የፕላስቲክ ቀዶ ህክምና ማሰልጠኛ ማዕከል በማቋቋም፣ ለሀገር ውስጥና ለተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ባለሙያዎች ስልጠና እየሰጠ መሆኑን አስታወቀ።

ማዕከሉ በአሁኑ ወቅት ከናይጄሪያ፣ ከሩዋንዳ፣ ከኬንያ፣ ከሶማሊያ፣ ከታንዛኒያ፣ ከቡሩንዲ እና ከማሊ ለመጡ የህክምና ባለሙያዎች በፕላስቲክ ቀዶ ህክምና ዘርፍ በንድፈ ሐሳብና ተግባር ስልጠናዎችን በመስጠት ላይ ይገኛል።

የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ ዶ/ር ሽመልስ ገዛኸኝ እንደገለጹት፤ ማዕከሉ ለጎረቤትና ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ባለሙያዎች ስልጠናውን የሚሰጠው በክፍያ በመሆኑ፣ ለተቋሙም ሆነ ለሀገሪቱ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ረገድ የጎላ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

ሆስፒታሉ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በፈጠረው ጠንካራ ትብብር፣ የራሱን ሐኪሞች ወደ ውጭ ሀገራት በመላክ የልምድ ልውውጥና የክህሎት ማሻሻያ ስልጠናዎችን እንዲያገኙ እያደረገ መሆኑን ዶክተር ሽመልስ አብራርተዋል።

ተቋሙ የጀመረውን ስኬታማ ጉዞ ይበልጥ ለማጠናከር ማዕከሉን ወደ ልህቀት ማዕከል የማሳደግ ሰፊ ዝግጅት እያደረገ የሚገኝ ሲሆን፤ ይህ የልህቀት ማዕከል ሲጠናቀቅ በፕላስቲክ ቀዶ ህክምና፣ በቆዳ፣ በአጥንት፣ በነርቭ ቀዶ ህክምና እና በልዩ የህፃናት ህክምና ዘርፎች የላቀ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል።

ለዚህም ግብ ስኬት የሚውል የህንፃ ግንባታ እና የዘመናዊ የህክምና ቁሳቁስ አቅርቦትን የማሟላት ስራዎች በከፍተኛ ፍጥነት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

ማዕከሉ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ሲገባ፣ ቀደም ሲል ለህክምና ወደ ውጭ ሀገር ይላኩ የነበሩና ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ የፕላስቲክ ሪኮንስትራክቲቭ ቀዶ ህክምናዎችን በሀገር ውስጥ ለማከናወን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።

ይህም በዘርፉ ያሉ ታካሚዎችን እንግልት ከመቀነስ ባለፈ፣ የሀገርን የህክምና ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ዶ/ር ሽመልስ ተናግረዋል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review