የባህር በር የቅርብ ጊዜ ፖለቲካዊ ፍላጎት ሳይሆን፣ ከኢትዮጵያ ህልውና ጋር የተጋመደ መሆኑን ሁሉም ሊረዳው ይገባል – ጀነራል ይመር መኮንን

You are currently viewing የባህር በር የቅርብ ጊዜ ፖለቲካዊ ፍላጎት ሳይሆን፣ ከኢትዮጵያ ህልውና ጋር የተጋመደ መሆኑን ሁሉም ሊረዳው ይገባል – ጀነራል ይመር መኮንን

AMN – መጋቢት 1/2018 ዓ.ም

ብሔራዊ የኢትዮጵያ ሰራዊት ማኅበር ያዘጋጀውና “ቀይ ባህርና የባህር በር”ን በተመለከተ ውይይት የሚደረግበት ሲምፖዚየም በዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ይገኛል። በሲምፖዚየሙ ላይ የተገኙት በኢፌዴሪ መከላከያ የትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ጀነራል ይመር መኮንን መልዕክት አስተላልፈዋል።

ጀነራሉ በመልዕክታቸው፣ “የባህር በር የቅርብ ጊዜ ፖለቲካዊ ፍላጎት ሳይሆን፣ ከኢትዮጵያ ህልውና ጋር የተጋመደ መሆኑን ሁሉም ሊረዳው እንደሚገባ ተናግረዋል። ቀይ ባህር ከጥንት ጀምሮ ከኢትዮጵያ ተነጥሎ እንደማያውቅ የገለጹት ጀነራል ይመር መኮንን፣ ባልተገባ ሁኔታ ከእናት ምድሩ መነጠሉ የሚያስቆጭ መሆኑን አንስተዋል። ይህ ስፍራ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም መሆኑን በመግለጽም፣ ይህን ማስከበር ከሀገር አልፎ ለቀጣናውም የላቀ ፋይዳ እንደሚኖረው አስረድተዋል።

በተለይም የቦታውን ጂኦስትራቴጂካዊ ፋይዳ ያብራሩት ጀነራሉ፤ የኢትዮጵያ በዚህ ስፍራ መገኘት ከራስ ባለፈ የቀጠናውን ሰላም የማረጋገጥ ሥራ እንድታከናውንም ያግዛታል ብለዋል። ብሔራዊ የኢትዮጵያ ሰራዊት ማኅበር ለዚህ ጉዳይ ትኩረት በመስጠቱ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር ታላቅ ክብር ይሰጣል ብለዋል።

የብሔራዊ የኢትዮጵያ ሰራዊት ማኅበር ፕሬዝዳንት ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ አማረ በበኩላቸው፣ ማኅበሩ በሀገር ደረጃ 305 ቅርንጫፎች ያሉት መሆኑን አንስተው፣ ሁልጊዜም ከሀገር፣ ከህዝብና ከመንግስት ጎን እንደሚቆም አረጋግጠዋል።

ለዓመታት ተዳፍኖ የቆየውን የባህር በር ፋይል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና መንግስታቸው ወደ አደባባይ በማውጣታቸው፣ ማኅበራችን የሚጠበቅበትን ለመወጣት ዝግጁ ነው ብለዋል።

በዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም እየተካሄደ በሚገኘውና ብሔራዊ የኢትዮጵያ ሰራዊት ማኅበር ባዘጋጀው በዚሁ ሲምፖዚየም ላይ ከጀነራል ይመር መኮንን በተጨማሪ፣ በመከላከያ የውጭ ግንኙነትና ወታደራዊ ትብብር ዳይሬክቶሬት ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል ተሾመ ገመቹ እና ሌሎችም ከፍተኛ የመከላከያ ሰራዊት አመራሮች ተገኝተዋል።

በበላይሁን ፍስሃ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review