የምድራችን አረንጓዴዋ ከተማ – ኩሪቲባ

You are currently viewing የምድራችን አረንጓዴዋ ከተማ – ኩሪቲባ

AMN-መጋቢት 01/2018ዓ.ም

በዓለም አቀፍ ደረጃ የከተሞች መስፋፋት ከተፈጥሮ መመናመን ጋር ተያይዞ የሚነሳ ስጋት ቢሆንም፣ የብራዚሏ ኩሪቲባ ግን ተቃራኒውን አስመስክራለች።

ኩሪቲባ እንደ አዲስ አበባ ሁሉ በአንድ ወቅት በትራፊክ መጨናነቅ፣ በቆሻሻ አወጋገድ እና በጎርፍ ችግር ትታመስ የነበረች ከተማ ነበረች። ነገር ግን በ1970ዎቹ የተነሳው የከተማዋ አመራር በስልታዊ መፍትሔ ከተማዋን የዓለም ተምሳሌት አድርጓታል።

ከተማዋ ባለፉት አምስት አሰርት ዓመታት ውስጥ ያሳየችው የተፈጥሮ ጥበቃ ጉዞ፣ ለብዙ የዓለማችን ከተሞች ታላቅ የፖሊሲና የፈጠራ ትምህርት የሚሰጥ ነው።

ኩሪቲባ ቀደም ሲል በከባድ ጎርፍ የምትታመስ ከተማ ነበረች። አብዛኞቹ ከተሞች እንዲህ አይነት ችግር ሲገጥማቸው ውድ የሆኑ የኮንክሪት ቦዮችን ለመገንባት ቢሮጡም፣ ኩሪቲባ ግን የተፈጥሮን መንገድ መረጠች።

የከተማዋ መሐንዲሶች ጎርፍ ሊያጠቃ የሚችለውን ዝቅተኛ መሬት ወደ ሰፋፊ ፓርኮችና ሰው ሰራሽ ሐይቆች ቀየሩት።
አሁን ላይ ዝናብ ሲዘንብ ውሃው ወደ መኖሪያ ቤቶች ከመግባት ይልቅ ወደነዚህ ሐይቆች ይፈሳል።

ዝናቡ ሲያቆም ደግሞ አካባቢው ለነዋሪዎች ማራኪ የመዝናኛ ስፍራ ይሆናል።
በዚህም ከተማዋ የጎርፍ መከላከያ ወጪዋን በመቀነስ፣ በአንድ ነዋሪ 52 ካሬ ሜትር አረንጓዴ ቦታ ማዳረስ ችላለች።

የተባበሩት መንግሥታት የሰፈራ ፕሮግራም ኩሪቲባን በፈጠራ የታጀበ የከተማ አመራርሞዴል አድርጎ ይጠቅሳታል። በዓለም ሰፈራ ዙሪያ ባወጣው ሪፖርትም የኩሪቲባን የፓርኮች ልማት እና የጎርፍ መከላከያ ስልት በምሳሌነት አቅርቦታል።

በደቡባዊ ብራዚል የምትገኘውና 2 ሚሊየን የሚጠጋ ነዋሪ ያላት ኩሪቲባ ፣ የቆሻሻ አወጋገድን ወደ ማህበራዊ ድጋፍ በመቀየር ብልሃት የተሞላው ስልትን ተጠቅማለች፡፡

“አረንጓዴ ልውውጥ” በተባለው መርሃ ግብር ፣ ነዋሪዎች ቆሻሻን ለይተው ሲያስረክቡ በምትኩ አትክልት፣ ፍራፍሬና የትራንስፖርት ትኬት ያገኛሉ። ይህም ከተማዋን ንጹሕ ከማድረጉ ባለፈ፣ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች የምግብ ዋስትና አረጋግጧል።

ዘጋርዲያን የከተሞች ታሪክ በሚል ተከታታይ ዘገባው ኩርቲባን የምድራችን አረንጓዴዋ ከተማ ሲል ገልጽዋታል፡፡

ኩሪቲባ ዛፍ መትከልን እንደ ግዴታ ብቻ ሳይሆን እንደ ኢኮኖሚያዊ ጥቅምም ትመለከተዋለች።

በግል ይዞታቸው ላይ ያሉ ዛፎችን ሳይቆርጡ ለጠበቁ ወይም አዳዲስ ዛፎችን ለተከሉ ነዋሪዎች የቤት ግብር ቅናሽ በማድረግ ታበረታታለች።

በተጨማሪም፣ በታሪካዊ ወይም በተፈጥሮ ስፍራዎች ላይ ግንባታ እንዳያካሂዱ የተከለከሉ ባለሀብቶች፣ በሌላ የከተማው ክፍል ከፍ ያሉ ፎቆችን እንዲገነቡ ልዩ ፈቃድ በመስጠት የግል ጥቅምና የከተማ ውበትን አጣጥማለች።

ኩሪቲባ የባቡር መስመር ለመዘርጋት የሚያስፈልገውን ከፍተኛ ወጪ መሸከም ስላልቻለች፣ አውቶቡሶችን እንደ ባቡር እንዲሰሩ አድርጋለች።

ተሳፋሪዎች ትኬት የሚቆርጡት በታዋቂዎቹ የመተላለፊያ “የቱቦ ጣቢያዎች” ውስጥ በመሆኑ፣ አውቶብሰ ሲመጣ በሰከንዶች ውስጥ ሰዎችን ጭኖ ይነሳል። ይህም የሕዝብ ትራንስፖርትን ከግል መኪና በበለጠ ፈጣንና ተመራጭ አድርጎታል።

የከተማዋ የተፈጥሮ ጥበቃ ስራ በግንባታ ብቻ አያበቃም። በአንድ ወቅት የድንጋይ ማውጫ በነበረ ስፍራ ላይ የተገነባው “የአካባቢ ጥበቃ ዩኒቨርሲቲ” ፣ ተራው ህዝብ ስለ ስነ-ምህዳር ሚዛን እንዲማር ያደርጋል። ህፃናትም ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ ቆሻሻን መለየትና ተፈጥሮን መንከባከብን በተግባር ይማራሉ።

አዲስ አበባ አሁን የጀመረችው የወንዝ ዳርቻ ልማትና የፓርኮች ግንባታ ከኩሪቲባ ጋር ተመሳሳይ መንፈስ አለው። የኩሪቲባ ተሞክሮ የሚያስተምረን ትልቁ ቁምነገር፣ ተፈጥሮን መጠበቅ “ቅንጦት” ሳይሆን የከተማን ህልውና የሚያረጋግጥና ወጪን የሚቀንስ ብልህ ስትራቴጂ መሆኑን ነው።

በታደሰ ሽፈራው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review