AMN – መጋቢት 1/2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ የበርካታ አነስተኛ ወንዞች ባለቤት ነች፡፡ አብዛኛው ወንዞቿ ግን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ለልማት የዋሉ፣ የነዋሪዎችን ኑሮ ያቃለሉ አልነበሩም፡፡
ይልቁንም በማኅበረሰቡና በአካባቢ ጤና ላይ የተለያዩ የጤና ጉዳቶችን ሲያስከትሉ የነበሩ ናቸዉ፡፡ ጥቂት የማይባሉ ወንዞችና ስዉር ቦታዎችም የወንጀለኞች መሸሸጊያ በመሆን በነዋሪዎች የደህንነት ስጋት ሆነው ቆይተዋል፡፡
ዛሬ ላይ ግን እነዚህ አካባቢዎች በኮሪደርና ወንዝ ዳርቻ ልማት አዲስ ገጽታን የተላበሱ ሲሆን ከጤናና በሰላም ወጥቶ ከመግባት ስጋት ተላቀዉ የመዝናኛና የቱሪስት መስህብ ለመሆን በቅተዋል፡፡
ከእነዚህ አካባቢዎች መካከል በቴዎድሮስ አደባባይ አካባቢ የሚገኘዉ የቁርጡሚ ወንዝ ተጠቃሽ ሲሆን የከተማ አስተዳደሩ አካባቢዉን ለዐይን ማራኪ እና ለቱሪስት መስህብ እንዲሆን አድርጎ ገንብቶታል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤም እጅግ ዘመናዊ ሆኖ የተገነባውን የድል ፕላዛ እና የቁርጡሚ የወንዝ ዳርቻ ልማትን ለአገልግሎት ክፍት አድረገዋል፡፡ በአንድ ወቅት የወንጀለኞች መሸሸጊያና የቆሻሻ መጣያ የነበረው ስፍራ፤ ዛሬ ውብ፣ ለዐይን ማራኪ እና የከተማዋ አንዱ የቱሪስት መስህብ ሆኖ መገንባቱንም ገልጸዋል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ
