AMN- መጋቢት 1/2018 ዓ.ም
በልደታ ክፍለ ከተማ “የመደመር መንግስት ዕይታ ስለ ሃይማኖት ተቋማት” በሚል መሪ ሀሳብ፣ በሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
መድረኩን የመሩት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ፣ ኢትዮጵያን በማጽናትና ትውልዱን በሥነ-ምግባር አንፆ ለማስቀጠል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን የነበራትን የመሪነት ሚና አጠናክራ ማስቀጠል እንዳለባት አስገንዝበዋል።
ኢንጂነር ወንድሙ በመልዕክታቸው፣ የጦር መሳሪያ ይዞ በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ መገኘት በፍጹም ሊወገዝ የሚገባው ተግባር መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
በመሆኑም የቤተ-ክርስቲያን መሪዎችና መምህራን እንዲህ ያሉ ድርጊቶችን አጥብቀው ሊቃወሙ እንደሚገባ አሳስበዋል።
አያይዘውም የእምነት ተቋማትን የፖለቲካ አመለካከት ማራመጃ ከማድረግ መቆጠብ እንደሚገባና ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር ተያይዞ ከሚፈጠሩ ውዥንብሮች ትውልዱን ለመታደግ መንግስትና የሃይማኖት ተቋማት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ የሃይማኖት አባቶች በበኩላቸው፣ የቤተ-ክርስቲያን ቀዳሚ ተልዕኮ ሰላምን ማወጅ መሆኑን ተናግረዋል። ወቅቱ የሱባኤና የጸሎት ጊዜ በመሆኑ ምዕመኑ በአሉታዊ ድርጊቶች ላይ ከመሳተፍ ይልቅ ጊዜውን በፆምና በጸሎት ሊያሳልፈው እንደሚገባ መክረዋል።
አባቶቹ አክለውም ያለችን ሀገር አንዲት በመሆኗ፣ ሰላሟ እንዲረጋገጥና የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በጽናት ለመቋቋም ከመንግስት ጋር በትብብር መሽራጽ እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ከቤተ-ክርስቲያኗ አባቶች ጋር የተጀመረ ይህ የውይይት መድረክ በቀጣይም ከሁሉም የእምነት ተቋማት ተወካዮች ጋር ተመሳሳይ ውይይቶች እንደሚደረጉ ዋና ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል።
በምትኩ ተሾመ