AMN – መጋቢት 01/2018 ዓ.ም
ዛሬ ከእጃችን የማይለየውና ዓለምን በትንሽ ስክሪን እንድንቆጣጠር ያስቻለን ስልክ፣ ከመቶ ሃምሳ ዓመታት በፊት በአንድ አነስተኛ ክፍል ውስጥ የተጀመረ “ተአምር” ነበር።
እ.ኤ.አ. መጋቢት 10 ቀን 1876 (መጋቢት 2 ፣ 1868 ዓ.ም) አሌክሳንደር ግራሃም ቤል ለረዳቱ ሚስተር ዋትሰን ያስተላለፈው “አቶ ዋትሰን፣ ወደዚህ ና፤ እፈልግሃለሁ” የሚለው ጥሪ፣ የሰውን ልጅ የመገናኛ ዘዴ ለዘላለም የቀየረ የታሪክ ምዕራፍ ከፈተ።
ከስልክ ፈጠራ በፊት የሰው ልጅ ግንኙነት በፈረስ ፍጥነት ወይም በቴሌግራፍ ምልክቶች የተገደበ ነበር። መረጃ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለመድረስ ቀናትን አንዳንዴም ሳምንታትን ይወስድ ነበር። ስልክ ግን ይህንን የጊዜና የቦታ ገደብ አሸነፈ።
ድምፅን በኤሌክትሪክ ሽቦ ውስጥ በማሳለፍ በቅጽበት ማድረስ መቻሉ፣ የሰውን ልጅ የመገናኘት ባህል ወደ አዲስ ምዕራፍ አሸጋገረው። የስልክ መምጣት ንግድና የከተማ እድገት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል።
ድርጅቶች መረጃ ለመለዋወጥ መልእክተኞችን ከመላክ ተላቀው በሰከንዶች ውስጥ ውሳኔ ማሳለፍ ጀመሩ። ይህም የዓለምን ምጣኔ ሀብት በማቀናጀት ረገድ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል።
በማህበራዊ ህይወትም ቢሆን፣ ቤተሰቦችና ወዳጆች በሺዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ቢራራቁም ድምፅ ለድምፅ በመስማማት ያላቸውን ቅርበት እንዲያጠናክሩ ረድቷቸዋል።
የቤል ፈጠራ ባለፉት 150 ዓመታት ውስጥ አስገራሚ ለውጦችን አስተናግዷል።

በጠረጴዛ ላይ ከሚቀመጥና በሽቦ ከሚገናኝ ስልክ ተነስተን፣ ዛሬ በኪሳችን በምንይዘውና ሁሉንም የኢንተርኔት መረጃዎች በያዘ “ስማርት ስልክ” ላይ ደርሰናል።
ቴክኖሎጂው ከድምፅ ግንኙነት ባለፈ ምስልን፣ መረጃንና የሰው ሰራሽ አስተውሎትን (AI) በማቀናጀት የሰው ልጅን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ የሚመራ መሣሪያ ሆኗል።
ዛሬ ስልካችንን ስናነሳ የምንሰማው ድምፅ ብቻ አይደለም፤ የ150 ዓመታት የሰው ልጅን የብልሃትና የጥበብ ውጤት ጭምር እንጂ።
የቤል ፈጠራ ዓለምን አንድ መንደር ከማድረጓም በላይ፣ የሰው ልጅ የማይደርስበት የቴክኖሎጂ ጥግ የሌለ መሆኑን ትልቅ ማረጋገጫ ሆና ትኖራለች።
በታደሠ ሽፈራው