AMN – መጋቢት 2/2018 ዓ.ም
የሃይማኖት ተቋማት የሀገረ መንግስትና የትውልድ ግንባታ መገንቢያ መሳሪያ ከመሆናቸው ባሻገር የሕዝብ ትስስር መፍጠሪያ መንገዶች መሆናቸውን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ጀማሉ ጀምበር (ዶ/ር) ገልጸዋል።
በጉለሌ ክፍለ ከተማ “የመደመር መንግስት ለሃይማኖት ተቋማት ያለው ዕይታ፣ አስተዳደራዊ መርሆዎች፣ ያጋጠሙ ችግሮችና የመፍትሔ አቅጣጫዎች” በሚል መሪ ሀሳብ ከእስልምና እምነት አባቶች ጋር የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
ኃላፊው እንደገለጹት የለውጡ መንግስት የዕምነት ተቋማት ነጻነትን በማክበር ሕገ መንግስቱን መሠረት በማድረግ በጋራ ሊያከናውኗቸው በሚገቡ ተግባራት ላይ አብረው ሲሠሩ በመቆየታቸው በከተማዋ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ዘርፎች ለተመዘገቡ ድሎች ሙስሊሙ ማሕበረሰብ ከመንግስት ጋር በመቀናጀት የበኩሉን ኃላፊነት ተወጥቷል።
ይህን ስኬት የበለጠ ለማጠናከር እና አልፎ አልፎ የሚስተዋሉ የአክራሪነት እና የጽንፈኝነት አስተሳሰብና ተግባራት ሰላማችንን የሚያናጉ በመሆናቸው አጥብቀን ልናወግዝና ልንቃወማቸው ይገባል ብለዋል።

የክ/ከተማው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወልዴ ወገሴ በበኩላቸው አስተዳደሩ ጉለሌን የለውጥ ተምሳሌት በማድረግ ሒደት ውስጥ የዕምነት ተቋማት ተሳትፎና ተጠቃሚነት እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
አሁንም የክ/ከተማውንም ሆነ የከተማውን ሰላምና ልማት ዘላቂ ለማድረግ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ከእስልምና ሃይማኖት ተቋማት ጋር በቅንጅት ልንሠራ ይገባል ብለዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ የተካፈሉት የእስልምና ሃይማኖት አባቶችም በለውጡ ያገኟቸውን ትሩፋቶች በማንሳት ይህን የመሩ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችን አመስግነዋል። እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ በሰላምና ልማት ዘርፎችም ከመግንስት ጋር በቅንጅት ለመሥራት ያላቸውን ቁርጠኝነትም አረጋግጠዋል።
በታምሩ ደምሴ