የማህበራዊ ሚዲያ መድረኮች በምርጫ ወቅት የተሳሳቱ መረጃዎች እና የጥላቻ ንግግሮች እንዳይሰራጭባቸው ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ተባለ

You are currently viewing የማህበራዊ ሚዲያ መድረኮች በምርጫ ወቅት የተሳሳቱ መረጃዎች እና የጥላቻ ንግግሮች እንዳይሰራጭባቸው ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ተባለ

AMN-መጋቢት 02/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ሚዲያ ባለስልጣን ከዓለም አቀፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ሜታ (Meta) ጋር በመተባበር፣ በምርጫ ዘገባ እና በዲጂታል መድረክ ህጎች ላይ ያተኮረ ስልጠና በመስጠት ላይ ነው ። ስልጠናው ጋዜጠኞች እና የዲጂታል ሚዲያ ባለሙያዎች በማህበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ የሚሰሯቸውን ዘገባዎች ተዓማኒነት፣ ሚዛናዊነት እና ደህንነት የተጠበቀ ለማድረግ ያለመ ነው።

በባለስልጣኑ የአቅም ግንባታ እና ስትራቴጂ ጉዳዮች መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ታምራት ደረጀ በመርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የማህበራዊ ሚዲያ መድረኮች ለዲሞክራሲያዊ ሂደትና ለነፃ መረጃ ፍሰት ያላቸው ሚና ከፍተኛ ቢሆንም፤ በተለይ በምርጫ ወቅት የተሳሳቱ መረጃዎች (Misinformation) እና የጥላቻ ንግግሮች የሚሰራጩባቸው መድረኮች እንዳይሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

በዚህም መሰረት ሜታ (ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም እና ዋትስአፕ) የሚከተላቸው የማህበረሰብ መመሪያዎች (Community Standards) ላይ ለስልጠና ተሳታፊዎች ሰፊ ገለፃ ተደርጓል።

በምርጫ ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ የዲጂታል ስጋቶችን እንዴት መለየትና መከላከል እንደሚችሉ፣ እንዲሁም የሜታ መድረኮችን በመጠቀም ትክክለኛ መረጃዎችን በፍጥነት ለህዝብ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ ስልቶችን ለሰልጣኞች በገለፃ ቀርቧል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የሚዲያ ባለሙያዎች በሜታ አጠቃቀም ላይ እያጋጠሙ ያሉ ተጨባጭ ችግሮችን በማቅረብ ከካምፓኒው ተወካዮች መልስ እና ማብራሪያዎች ተሰጥቷል።

የስልጠናው ተሳታፊዎች ስልጠናው የሚዲያ ባለሙያዎችን አቅም ከመገንባት ባለፈ፣ ፕላትፎርሞቹን በመጠቀም በሀገሪቱ ግልጽ የሆነ የምርጫ መረጃ ልውውጥ እንዲኖር መሰረት ይጥላል ብለዋል።

ባለሙያዎቹ ከስልጠናው ያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር በመቀየር፣ ሃላፊነት የተሞላበት የዲጂታል ጋዜጠኝነትን እንዲያራምዱ ጥሪ ቀርቧል።

በሹመት ደመቀ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review