የመዲናዋን የትራንስፖርት አገልግሎት በቴክኖሎጂ ለማዘመን እየተሠራ ነው – የትራንስፖርት ቢሮ

You are currently viewing የመዲናዋን የትራንስፖርት አገልግሎት በቴክኖሎጂ ለማዘመን እየተሠራ ነው – የትራንስፖርት ቢሮ

AMN- መጋቢት 2/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የመዲናዋን የትራንስፖርት አገልግሎት በዘላቂነት ለማዘመንና በመሠረተ ልማት ረገድ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት የሚያስችሉ መጠነ ሰፊ የሪፎርም ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ ዳኛቸው ሽፈራው ለኤ ኤም ኤን እንደገለጹት፣ ቢሮው በኮሪደር ልማት የታገዙ የመንገድ ስራዎችን፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምንና የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያዎችን በትኩረት እየተገበረ ይገኛል።

እንደ ምክትል ኃላፊው ማብራሪያ፣ ቀደም ሲል በከተማዋ በስፋት ይታዩ የነበሩት የመንገድ ጥበት፣ የእግረኛ መንገዶች እጥረትና የተሽከርካሪ ማቆሚያ ችግሮች በአሁኑ ወቅት በኮሪደር ልማቱ አማካይነት መሠረታዊ ለውጥ ተደርጎባቸዋል።

ይህ አዲሱ አሠራር የአገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋና ፍትሐዊ ለማድረግ የላቀ ሚና እንዳለው የገለጹት አቶ ዳኛቸው፣ የብዙኃን ትራንስፖርት ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ በመምጣቱ የአውቶቡስ አቅርቦትን በማሳደግ የዜጎችን እንግልት ለመቀነስ በትኩረት እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ይህ የማሻሻያ ሥራ የከተማዋን ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆን ከከተማዋ ጋር የቅርብ ትስስር ያላቸውን ዙሪያ ገብ ከተሞች ነዋሪዎችንም ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አብራርተዋል።

በሌላ በኩል፣ አዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኙት 48 ተርሚናሎኖች መካከል በቀን ከ150 ሺህ እስከ 200 ሺህ የሚደርሱ ተጓዦችን የሚያስተናግደው የመገናኛ ተርሚናል በኮሪደር ልማቱ ያልተካተተ በመሆኑ ሰፊ ማሻሻያ እንደሚሻ ምክትል ኃላፊው አመልክተዋል።

በመሆኑም በተርሚናሉ የሚታየውን መጨናነቅና የተጓዦችን የረጅም ሰዓት ጥበቃ ለመፍታት፤ በየካ ክፍለ ከተማና በሌሎች አቅራቢያ አካባቢዎች አዳዲስ ተርሚናሎችን የመገንባት ስራ መጀመሩን አስታውቀዋል።

በተለይም ወደ አራብሳ፣ ጣፎ፣ አያት፣ ሳር ቤትና ኮዬ ፈጬ ለሚጓዙ ዜጎች ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት የተሽከርካሪዎች ቁጥር እንዲጨምር መደረጉን ም/ቢሮ ኃላፊው ገልጸዋል።

ምሽት ላይ የሚታየውን የትራንስፖርት እጥረት ለመቅረፍም ከምሽቱ 1፡30 እስከ 2፡00 ሰዓት ተጓዦች ሙሉ በሙሉ አገልግሎት እንዲያገኙ ጥረት እየተደረገ ሲሆን፤ ከዚያ በኋላም የምሽት ትራንስፖርት አገልግሎት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የቅርብ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review