AMN- መጋቢት 2 /2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ዛሬ በልደታ ክፍለ ከተማ የገነባነውን ዘመናዊ ባለ 4 ወለል የመኖሪያ ህንፃ፣ ለማህበራዊ ችግር ለተጋለጡ ወገኖች፣በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ፣ ለአካል ጉዳተኞች እና ለሀገር ባለዉለታ ለሆኑ ነዋሪዎቻችን “ቤት ለእምቦሳ” ብለን በክብር አስረክበናል ብለዋል።
በተጨማሪም በተለያዩ የልማት ስራዎች የተነሱ በቀበሌ ቤት ውስጥ በደባልነት፣ በጥገኝነትና በላስቲክ ቤት ውስጥ እና የመፀዳጃ ቤት ፍሳሽ በላያቸዉ እያለፈ እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ለነበሩ ወገኖቻችን ጭምር ቤት አስረክበናል ሲሉ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።
አዲስ ሰበባ በሰዉ ተኮር ስራዎቿ ተምሳሌት ሆናለች ያሉት ከንቲባዋ፣ ሰዉ ተኮር ስራዎችን ጠቅላይ ሚኒስትራችን አስጀምረዉ በርትተን እንድንሰራ የስራ መመሪያ ከሰጡበት ጊዜ ጀምሮ ላለፋት 7 ዓመታት በሰዉ ተኮር እሳቤያችን እና በበጎነት አገልግሎት ተሳትፎ ከ45 ሺህ በላይ ቤቶችን ለአቅመ ደካሞች መገንባት ችለናል ብለዋል።

በጎ ፈቃደኞችን በማስተባበር በ4 ወራት አጭር ጊዜ ውስጥ የተገነባው ይህ የመኖሪያ ቤት፤ 5 ነባር ቤቶችን በማንሳት 70 አባወራዎችን ቤት እንዲገኙ ያደረገ ነው።
ይህም ከእጦት መንፈስ ወጥተን ቦታን በአግባቡ በመጠቀም ትልቅ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል የሚሳይ ሲሆን፣ በከፍተኛ የጥራት ደረጃ ተገንብቷል ብለዋል።
ግንባታው የጥራት ደረጃውን የጠበቀ፣ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ፣ የዜጎችን ክብር የሚመጥንና የቤት ቁሳቁስ የተሟላለት ዘመናዊ ህንፃ ነው።
ከተማችን ለሁላችንም ትበቃለች፤ መተሳሰብና ፍቅር ካለ ደግሞ ይበልጥ መስራት ይቻላል ያሉት ከንቲባዋ፣ በቀጣይም ለብዙዎች ለመድረስ በትጋት እንሰራለን ብለዋል።
ይህን እጅግ ዘመናዊና የዜጎችን ክብር የሚመጥን የመኖሪያ ቤት ግንባታ በማስተባበር ለተሳተፋችሁ ተቋማት፣ ባለሀብቶችን ላስተባበሩት የከንቲባ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ጥላሁን ወርቁ፣ ለደገፋችሁ ባለሀብቶችና ድርጅቶች በሙሉ ከልብ የመነጨ ምስጋናዬን አቀርባለሁ በማለትም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።