ጎግል አማርኛ እና አፋን ኦሮሞን ጨምሮ 13 የአፍሪካ ቋንቋዎችን በኤአይ አገልግሎቱ አካተተ

You are currently viewing ጎግል አማርኛ እና አፋን ኦሮሞን ጨምሮ 13 የአፍሪካ ቋንቋዎችን በኤአይ አገልግሎቱ አካተተ

AMN — መጋቢት 2/2018 ዓ.ም.

ግዙፉ የቴክኖሎጂ ተቋም ጎግል በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የታገዘውን የመረጃ መፈለጊያ አገልግሎቱን አማርኛ እና አፋን ኦሮሞን ጨምሮ 13 የአፍሪካ ቋንቋዎችን በአገልግሎቶቹ ማካተቱን አስታውቋል።

ጎግል በሰው ሰራሽ አስተውሎት የታገዘውን የመረጃ መፈለጊያ አገልግሎቱን በበርካታ ቋንቋዎች በመተግበሪያው ላይ ማካተቱ ቴክኖሎጂ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ላይ ብቻ ተወስኖ የሚቀርበት ዘመን እያበቃ መሆኑን ያበሰረ ነው ብሎታል።

ኩባንያው እነዚህን ቋንቋዎች በኤአይ (AI) የፍለጋ ዘዴው ውስጥ መቀላቀሉ፣ በአፍሪካ አሕጉር የጀመረውን የዲጂታል አገልግሎት የማስፋፋት ዕቅድ ለማሳካት ያስችለዋል።

ይህ አዲስ ማሻሻያ የጎግል የኤአይ መረጃ መፈለጊያ ለሀገር በቀል ቋንቋዎች ድጋፍ እንዲሰጥ የሚያደርግ ሲሆን፣ ተጠቃሚዎች በጽሑፍ፣ በድምጽ ወይም በምስል በሚፈልጉት ቋንቋ መረጃዎችን በቀላሉ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል።

በጎግል አዲስ የተካተቱት የአፍሪካ ሀገር በቀል ቋንቋዎች አማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ፣ ሶማሊኛ፣ አፍሪካንስ፣ አካን፣ ሃውሳ፣ ኪንያርዋንዳ፣ ኪስዋሂሊ፣ ሴሶቶ፣ ሴትስዋና፣ ዎሎፍ፣ ዮሩባ እና ኢሲዙሉ ሁሉም ዜጋ በራሱ ቋንቋ መረጃ እንዲያገኝ አዲስ ዕድል ፈጥረዋል።

እነዚህ ቋንቋዎች የተመረጡት በአፍሪካ በስፋት የሚነገሩ በመሆናቸውና በቋንቋው ተጠቃሚዎች የሚስተዋለውን ከፍተኛ የዲጂታል አገልግሎት ፍላጎት ታሳቢ በማድረግ እንደሆነ ጎግል ገልጿል።

ተጠቃሚዎች ቀደም ሲል በጎግል መተርጎሚያ በጽሑፍ ብቻ ይገለገሉ የነበሩትን የኤአይ አገልግሎቶችን፣ አሁን ላይ አፍሪካውያን በራሳቸው ቋንቋዎች በድምጽና በምስል ጭምር በመታገዝ ውስብስብ መረጃዎችን በቀላሉ እንዲፈልጉና እንዲያገኙ ያስችላቸዋል።

Connecting Africa ድረ ገጽ እንደዘገበው ኢትዮጵያ የዲጂታል ቴክኖሎጂን እያበረታታች ባለችበት በዚህ ወቅት፣ ጎግል ይህንን እርምጃ መውሰዱ ሀገሪቱ የያዘችውን ስትራቴጂ ለማሳካት ትልቅ ግብዓት ይሆናል።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review