AMN – መጋቢት 2/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፉት ጥቂት ዓመታት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ያስገነባቸውን ከ45 ሺህ በላይ የመኖሪያ ቤቶች ለተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ማስተላለፉን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባዋ ይህንን ያስታወቁት በልደታ ክፍለ ከተማ ሳር ቤት አካባቢ፣ በከንቲባ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪነትና በባለሀብቶች ድጋፍ የተገነቡ መኖሪያ ቤቶችን ለነዋሪዎች ባስረከቡበት ወቅት ነው።
ቤቶቹ የተላለፉላቸው ለተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮች ለተጋለጡ፣ ለሀገር ባለውለታዎችና በፈራረሱ ቤቶች ውስጥ ለሚኖሩ ዜጎች መሆኑ ታውቋል።
የመኖሪያ ቤት ጥያቄ የከተማዋ አንገብጋቢ ችግር መሆኑን የጠቀሱት ከንቲባ አዳነች፣ በተለይም አሮጌና በጭቃ በተሠሩ የቀበሌ ቤቶች ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች ለከፍተኛ ስቃይ ተጋልጠው እንደነበር አስታውሰዋል።

ፍሳሽ በላያቸው ላይ እየፈሰሰና በሰቀቀን ውስጥ የሚኖሩ እናቶችን ችግር ለመቅረፍ የተከናወነው ይህ ተግባር፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተጀመረው የ”ሰው ተኮር” ልማት መርሃ ግብር አካል መሆኑን አብራርተዋል።
በከተማዋ የተጀመረው አዲስ የቦታ አጠቃቀም እይታ በአነስተኛ ቦታ ላይ በርካታ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ ከንቲባዋ ገልጸዋል። ለአብነትም ቀደም ሲል አምስት ቤቶች ብቻ በነበሩበት ቦታ ላይ፣ አሁን 70 አባወራዎችን ማስተናገድ የሚችል ዘመናዊ ሕንፃ መገንባት ተችሏል ብለዋል።
እስካሁን ባለው ሂደት ከ100 ሺህ በላይ ዜጎች ከነበሩበት የተጎሳቆሉ ቤቶች ወጥተው የተሻለ ኑሮ እንዲመሩ መደረጉን የገለጹት ከንቲባዋ፣ ለዚህ ስኬት ከፍተኛ ድጋፍ ላደረጉ ባለሀብቶችና በጎ ፈቃደኞች ምስጋና አቅርበዋል።
በበረከት ጌታቸው