AMN – መጋቢት 2/2018 ዓ.ም.
መካከለኛው ምሥራቅ የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ የተፈጠረውን የነዳጅ ቀውስ ለመፍታት የመፍትሔ እርምጃዎች እየወሰደች እንደምትገኝ የገንዘብ ሚኒስቴር ገለጸ።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ እንደገለጹት መንግሥት የነዳጅ አቅርቦትን አስተማማኝ ለማድረግ እና የመግዛት አቅምን ያማከለ እንዲሆን ከፍተኛ ድጎማ እያደረገ ይገኛል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተውን የነዳጅ ቀውስ ለመቋቋምም በነዳጅ ምርት ላይ ይደረግ የነበረውን ድጎማ ከፍ በማድረግ እያቀረበ እንደሚገኝ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነትን ተከትሎ የሆርሙዝ ሰርጥ በመዘጋቱ ሳቢያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዋጋው ያሻቀበ ቢሆንም፣ መንግሥት ከፍተኛ ድጎማ በማድረግ መጠነኛ የዋጋ ማሻሻያ ብቻ በማድረግ ለገበያ እያቀረበ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በሆርሙዝ ሰርጥ መዘጋት ምክንያት የነዳጅ አቅርቦት እጥረት እንዳይፈጠርም መንግሥት ተጨማሪ የነዳጅ ግዥ እየፈጸመ ይገኛል።
ትላንት የተደረገው የዋጋ ማሻሻያ አሁን ካለው የነዳጅ ገበያ አንጻር ከፍተኛ ድጎማ የተደረገበት እንደሆነ ገልጸዋል ሚኒስትሩ።
አስቀድሞ 53 ብር ከ68 ሣንቲም ይደጎም የነበረው የነጭ ናፍጣ ዋጋ ዛሬ ላይ 238 ብር ከ13 ሣንቲም በሊትር ቢደርስም፣ መንግሥት 98 ብር ድጎማ በማድረግ በ139 ብር ከ84 ሣንቲም ለኅብረተሰቡ እያቀረበ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በተመሳሳይ መንግሥት በሊትር 28 ብር ከ77 ሣንቲም ይደጉም የነበረው የቤንዚን ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ በማሳየት ዛሬ ላይ በሊትር 205 ብር ከ74 ሣንቲም በዓለም ደረጃ እየተሸጠ ቢገኝም፤ ለኅብረተሰቡ በሊትር 73 ብር ከ56 ሣንቲም በመደጎም በ132 ብር ከ18 ሣንቲም እየቀረበ እንደሚገኝ አንሥተዋል።
መንግሥት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ድጎማ የሚያደርግበት ይህ የነዳጅ አቅርቦት፣ ከተቀመጠለት ዋጋ ውጭ እና ከአቅርቦት ሰንሰለት ውጭ ባልተገባ መንገድ ለገበያ እየቀረበ እንደሚገኝ በጥናት መለየቱን ተናግረዋል።
ይህንን ሕገ-ወጥ ተግባር ለመከላከልም በዚህ ውስጥ በተሳተፉ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን አስታውቀዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተውን ቀውስ ለመቋቋም መንግሥት አጣዳፊ ግዥዎችን ጨምሮ ከተቀመጠው መጠባበቂያ ክምችት ጭምር ወደ ገበያ እንዲገባ በማድረግ የመፍትሔ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል።
ኅብረተሰቡ ከአቅርቦት ሰንሰለት ውጭ የሚደረግ ግብይትን በመከላከል ከፀጥታ አካላት ጋር በትብብር ሊሠራ ይገባል ያሉት ሚኒስትሩ፤ በነዳጅ አጠቃቀም ላይ ቁጠባ ሊደረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።