AMN መጋቢት 3/2018 ዓ.ም
ከዐቢይ እና ረመዳን ጾም ወቅቶች ጋር በተያያዘ ካለዉ ከፍተኛ የምርት ፍላጎት አንጻር ከ3 ሚሊዮን ሊትር በላይ ዘይት ለማቅረብ እየሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ የንግድ ስራዎች ድርጅት አስታወቀ፡፡
የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መስፍን አሰፋ ለኤኤምኤን እንደገለጹት፣ በተለይ በአጽዋማት እና በበአላት ወቅት ሊኖር የሚችለዉን የምርት የፍላጎት መጨመር ከግምት ዉስጥ በማስገባት ደርጅቱ የአቅርቦት መጠኑን በእጥፍ ጨምሯል፡፡
በመዲናዋ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የሸማቾች ማዕከላትም ዘይትን ጨምሮ የኢንዱስትሪና የምግብ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ፡፡
ባለፉት ስምንት ወራት ከበአላት ወቅት ዉጪ በአማካይ አንድ ሚሊዮን ሊትር ዘይት እያቀረብን ነዉ ያሉት ኃላፊዉ ከበአላት ጋር በተያያዘም ተጨማሪ ምርቶች እየቀረቡ ነዉ፡፡

ከዐቢይ እና ረመዳን ጾም ወቅቶች ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የምርት ፍላጎት ስላለ በሚቀጥሉት አራት እና አምስት ሳምንታት 3.1 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ለማቅረብ እየተሰራ ነዉ ብለዋል፡፡
ምርቶቹ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ለማህበረሰቡ እንዲቀርቡ ከሕብረት ሥራ ማህበራት እና ከሌሎች የግል እና መንግስታዊ ተቋማት ጋር በትብብር እየተሰራ ነዉ፡፡
ከገበያ አንጻር በደርጅቱ የሚቀርቡ ምርቶች ተመጣጣኝና ከገበያ አንጻርም ዝቅተኛ መሆናቸዉን የተናገሩት ዋና ስራ አስኪያጁ ዘይት ከመደበኛ ገበያ አንጻር ከ500 – 700 ብር ፤ ሌሎች ምርቶች ደግሞ ከ20 – 30 በመቶ የሚደርስ የዋጋ ልዩነት እንዳላቸዉ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በአዲስ አበባ የንግድ ስራዎች ድርጅት የምርት ሽያጭ እና ስርጭት ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ሙላቱ በበኩላቸዉ በበአላት ወቅት የሚያስፈልጉ ምርቶችን በማጥናት እና ግዢ በመፈጸም የማጓጓዝ ሂደት መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡
ድርጅቱ የተለያዩ ምርቶችን በተመጣጣኝ እና ዝቅተኛ ዋጋ ለሸማቾች ለማቅረብ ከአርሶ አደሮችና ከአምራቾች ጋር በመቀናጀት በቀጥታ እየሰራ የሚገኝ ሲሆን በመዲናዋ የተለያዩ አካባቢዎች የምርት ማከማቻ እና ማከፋፈያ ማዕከላት እንዳሉት ከድርጅቱ ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ