AMM – መጋቢት 3/2018 ዓ.ም
17ኛው ከተማ አቀፍ አዲስ የኪነ-ጥበብ ፌስቲቫል ሳምንት ከመጋቢት 5 እስከ 7 2018 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ እንደሚካሄድ የአዲስ አበባ ባህልና ኪነ-ጥበብ ቢሮ ገለጸ።
ቢሮው 17ኛውን ከተማ አቀፍ አዲስ የኪነ-ጥበብ ፌስቲቫል ሳምንት አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
ፌስቲቫሉ “የጥበብ ስጦታ ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል ከመጋቢት 5 እስከ 7- 2018 ዓ.ም እንደሚካሄድ በቢሮው የኪነ-ጥበብ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ ሉባባ ጅማል ገልጸዋል።
በዚሁ ጊዜ ኪነ-ጥበብ ለህብረ-ብሔራዊነት እና ለገዥ ትርክት ያለው ፋይዳ የጎላ መሆኑን ሃላፊዋ ጠቅሰዋል።

እንዲሁም ፌስቲቫሉ በኪነ-ጥበብ ዘርፍ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ባለሞያዎች ችሎታቸውን እንዲያሳዩ እና ተተኪ የኪነ-ጥበብ ባለሞያዎችን ለማፍራት እንደሚያስችል ገልጸዋል።
የከተማዋን አዲስ ገጽታ ለማስተዋወቅም የፌስቲቫል ሳምንቱ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረውም አብራርተዋል።
በከተማ አቀፍ የኪነ-ጥበብ ፌስቲቫሉ ከ250 ሺህ በላይ ነዋሪዎች እንደሚሳተፉ ተጠቅሶ፣ በ16 የኪነ-ጥበብ ዘርፎች ውድድር እንደሚካሄድ በመግለጫው ተመልክቷል።
በዳንኤል መላኩ