AMN- መጋቢት 03/2018 ዓ.ም
መገናኛ ብዙሃን ለብሔራዊ ጥቅም በሚል መርህ የመገናኛ ብዙሃንና የተቋማት አመራሮች የተሳተፉበት ሀገር አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት አባቶቻችን ኢትዮጵያን በጋራ እሳቤዎች ጠብቀው ለዛሬው ትውልድ አቆይተዋል ስለሆነም የመገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅሞችን በማስጠበቅ ፣ህብረ ብሄራዊ አንድነት በማጠናከር ፣የወል ትርክትን በመገንባትና የብልጽግና ዕሳቤዎችን በመፍጠር ከመቼውም በላቀ ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የመገናኛ ብዙሃን በአዋጅ የተሠጣቸውን ሀገራዊ ሃላፊነት ከፍተኛ ሚና እየተወጡ እንደሚገኙ የጠቀሱት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሃይማኖት ዘለቀ ናቸው ።
ከለውጡ ጀምሮ መንግስት የመገናኛ ብዙሃን የመረጃ ነጻነታቸው ተጠብቆ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ በርካታ ሥራዎችን ሠርቷል ብለዋል።
በቀጣይም ኢትዮጵያ የምትከተለውን የሠላምና የልማት አቅጣጫዎችን በመገንዘብ በማህበራዊ ሚድያዎች የሚሠራጩ የታሪካዊ ጠላቶችን አፍራሽ መረጃዎችን በመቀልበስና ለብሄራዊ ጥቅሞች ተሟጋችና ዘብ ሆነው ሊቆሙ ይገባል ሲሉ ዋና ዳይሬክተሯ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል ።
በአለሙ ኢላላ