የምሽት መብራቶች – የሥልጣኔና የዘመናዊ ከተሞች መገለጫ

You are currently viewing የምሽት መብራቶች – የሥልጣኔና የዘመናዊ ከተሞች መገለጫ

AMN መጋቢት 3/2018 ዓ.ም

ዘመናዊ የምሽት መብራቶች ከተሞችን ይበልጥ ደማቅ፤ ብርሃናማ እና ለእይታ ማራኪ እንዲሆኑ ከማድረግ ረገድ ያላቸዉ ድርሻ የላቀ ነዉ፡፡

በመብራት የደመቁ ከተሞች በተለይ ከከፍታ ላይ ወደታች ሲታዩ የስነ-ህንፃ ውበትን እና ዘመናዊነትን ይበልጥ ይገልጣሉ፡፡ ለፎቶ ግራፍ፤ ለቪዲዮና መሰል ኩነቶችም እጅግ የሚመቹ ናቸዉ፡፡

በምሽት መብራቶች የተሻለ ተሞክሮ ካላቸዉ የአለማችን ሃገራት መካከል የህንድ፤ የጃፓን እና ብራዚል ዋና ከተሞች በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡

የሀንጋሪ፤ ሜክሲኮ እና ቤልጂየም ከተሞችም በስነ-ህንፃ ጥበብ ምርጥ ከሚባሉ የአለማችን ከተሞች መካከል ዋንኞቹ ናቸዉ፡፡

መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ በሰማይ ጠቀስ ህንጻዎቻቸዉ በምሽት ደምቀዉ ከሚታዩት የአለማችን ከተሞች መካከል ዱባይ፤ ሻንጋይ እና ላስ ቬጋስ የተሻለ ተሞክሮ አላቸዉ፡፡

የኢትዮጵያ ብሎም የአፍሪካ መዲና የሆነችዉ አዲስ አበባ ከቅርብ አመታት ወዲህ በኮሪደርና ወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎች አዲስ ገጽታን የተላበሰች ሲሆን በተለይ የምሽት መብራቶቿ የበርካቶች መነጋገሪ ሆነዋል፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከኡራኤል – ቦሌ መድሃኔአለም እስከ ቦሌ ድልድይ ያለዉን የኮሪደር ልማት መርቀዉ ስራ ባስጀመሩበት ወቅት እንደገለጹት በመዲናዋ የተከናወኑት የኮሪደርና ወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎች ጽዱ፤ ለመኖር ምቹ እና ለእይታ የሚማርኩ አካባቢዎችን ፈጥረዋል፡፡

ከተሞችን እና ህንጻዎችን በዘመናዊ የምሽት መብራቶች ማስዋብ እና ማድመቅ አለማቀፍ ተሞክሮ መሆኑን ያነሱት ከንቲባዋ ይህንኑ ለመመልከት ወደ ተለያዩ የአለም ከተሞች የሚሄዱ ዜጎች እንዳሉም አንስተዋል፡፡ ብርሃን የሚወደድ እንጂ የሚጠላ አይደለም፤ ጨለማ የወንጀለኞች መደበቂያ ነዉ፤ የምሽት የንግድ እንቅስቃሴንም ያዳክማል ብለዋል፡፡

በመዲናዋ በተለያዩ ኮሪደሮች የተከናወኑ የልማት ስራዎች የመዲናዋን ገጽታ ከመቀየራቸዉም በላይ ለቱሪስት መስህብነት እያገለገሉ መሆናቸዉንም ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል፡፡

በቅርቡ አዲስ አበባን የጎበኘዉ አይሾዉስፒድን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ እና የአለማችን ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፤ ታዋቂ ሰዎች እና መሪዎች ከቅርብ አመታት ወዲህ በመዲናዋ የተከናወኑ የኮሪደርና ወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎችን ማድነቃቸዉ የሚታወስ ነዉ፡፡

አሁን ላይ በአዲስ አበባ በምሽት መንቀሳቀስም ሆነ መዲናዋን መጎብኘት፤ የንግድ ስራዎችን መከወን፤ የተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን መስራትና በመሰል ስራዎች ላይ መሰማራት የከተሜነትና የዘመናዊነት መገለጫ ሆኗል፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review