አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በጋሞ ዞን በመሬት መንሸራተት የተጎዱ ወገኖችን አጽናኑ

You are currently viewing አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በጋሞ ዞን በመሬት መንሸራተት የተጎዱ ወገኖችን አጽናኑ

AMN – መጋቢት 04/2018 ዓ.ም

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ በጋሞ ዞን በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖችና ለሟች ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኙ።

አፈ ጉባኤው በትላንትናው ዕለት የኩልፎ ወንዝ ሙላት በአርባ ምንጭ ከተማ በሚገኙ ነዋሪዎች ንብረቶችና መሠረተ ልማቶች ላይ ያደረሰውን ከፍተኛ ጉዳት በአካል ተገኝተው የተመለከቱ ሲሆን፣ በዛሬው ዕለት ደግሞ ለማፅናኛ በተዘጋጀ ስፍራ በመገኘት ለተጎጂ ቤተሰቦች ያላቸውን አጋርነት ገልጸዋል።

በዚሁ የማፅናኛ መርሃ ግብር ላይ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደን ጨምሮ የክልሉ፣ የጋሞ ዞንና የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል። ኃላፊዎቹ በአደጋው የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን በመግለጽ፣ ከመንግሥት ጎን በመሆን ለተጎጂዎች አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።

በጋሞ ዞን በሚገኙ አራት ወረዳዎች በተከሰተው በዚህ አስከፊ የመሬት መንሸራተት አደጋ እስካሁን የ70 ሰዎች ሕይወት ማለፉ የተረጋገጠ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የአስክሬን ፍለጋ ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገልጿል።

ሆኖም የፍለጋ ሂደቱ ገና ባለመጠናቀቁ የሟቾች ቁጥር ከዚህም ሊበልጥ እንደሚችል ምክር ቤቱ ለኤ ኤም ኤን በላከው መረጃ አመላክቷል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review