AMM – መጋቢት 4/2018 ዓ.ም
“መገናኛ ብዙኃን ለብሔራዊ ጥቅም” በሚል መሪ ሀሳብ በተዘጋጀው አገራዊ ኮንፈረንስ ላይ የተገኙት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፤ ሊቢያ ከውድመት በኋላ የገባችበትን አስከፊ ሁኔታና የዜጎቿን ጥልቅ ጸጸት በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል።
አገራችሁን አፍርሱ ያሏቸው ሰዎች ካፈረሱ በኋላ አላገኟቸውም፤ እነሱ ግን የፈረሰች አገር ታቅፈው ቀርተዋል ሲሉ የውጭ ጣልቃ ገብነትና ያልተገደበ ስሜት ያስከተለውን ዘላቂ ጥፋት አብራርተዋል።
አማካሪው በቅርቡ ወደ ሊቢያ ባደረጉት ጉዞ ከአገሪቱ የሀገር ሽማግሌዎች ጋር በነበራቸው ቆይታ የታዘቡትን መራራ እውነት ሲያጋሩ፤ ሊቢያውያን አገሪቱ ከመፍረሷ በፊት ይነገራቸው የነበረው የዲሞክራሲ፣ የፍትሐዊነት እና የብልጽግና ተስፋ ዛሬ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ፍጹም ተቃራኒ ሆኖ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
በተለይም ሊቢያ ከለውጥ በኋላ ነጻ እንደምትወጣና ማርና ወተት የምታዘንብ ምድር እንደምትሆን ቃል ተገብቶላቸው እንደነበር ያስታወሱት ዲያቆን ዳንኤል፤ ሽማግሌዎቹ ዛሬ ግን በከፍተኛ የጸጸት ስሜት ውስጥ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
አማካሪው አክለውም ሊቢያውያን ለለውጥ በሚል ስም አገራቸውን እንዲያፈርሱ በወቅቱ ግፊት ሲያደርጉባቸው የነበሩ አካላት ዛሬ አብረዋቸው አለመኖራቸውን ገልጸዋል።
ሊቢያ ቀደም ሲል የነበረችበት የዕድገት ደረጃ ሌላ ዓለም እንደነበረ ያስታወሱት አማካሪው፣ ዛሬ ግን ዜጎች የሚታጠቡ አስፋልቶችንና ዘመናዊ ሆቴሎችን በፎቶግራፍ እያዩ በትዝታ እንደሚቆዝሙ ገልጸዋል።
አገሪቱ ብትፈራርስም፣ የሊቢያ ምርጥ ነዳጅ አሁንም በሁለቱ ትላልቅ ወደቦቿ በኩል ሳይቋረጥ እየተጫነ እንደሚወጣ በአካል መመልከታቸውን ዲያቆን ዳንኤል ተናግረዋል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች አገራት የድሮው የፈረሰ ፎቶ በአዲሱ የለማ ፎቶ ሲተካ፣ በሊቢያ ግን በተቃራኒው የድሮው ያማረ ፎቶ በአሁኑ በፈራረሰው ፎቶ እየተተካ ነው ሲሉ አማካሪው በንፅፅር ገልጸዋል።
ይህም የሀገር ብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ በውል ካልተያዘ የሚያስከትለውን ውድመት ትልቅ ማሳያ መሆኑን አማካሪው አስገንዝበዋል።
በበረከት ጌታቸው