AMM – መጋቢት 4/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚታዩ ስር የሰደዱ ተግዳሮቶችን ለመፍታትና ምቹ የንግድ ከባቢ ለመፍጠር ያለመ የምክክር መድረክ አካሄደ።
በውይይቱ ላይ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት፣ የንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮች እና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ዘሀራ መሐመድ እንደገለጹት፤ የንግዱን ማህበረሰብ በተለይም በግሉ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶችን ለማነቃቃት ሰፊ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም፣ አሁንም ድረስ የመሬትና የፋይናንስ አቅርቦት እጥረት እንዲሁም አስተዳደራዊ ቢሮ ክራሲዎች ለዘርፉ እድገት ትልቅ ማነቆ ሆነው ቀጥለዋል።
እነዚህን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታትም ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር በቅንጅት መስራት የግድ እንደሚል አስገንዝበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጳውሎስ ኩሳባ በበኩላቸው፣ መንግስት የባለሀብቶችን ጥያቄ ለመመለስ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል።

በከተማዋ የተለያዩ ክፍለ ከተሞች በርካታ ሄክታር መሬቶችን ለኢንቨስትመንት ዝግጁ የማድረግ ስራ እየተከናወነ መሆኑንና የኢንዱስትሪ ሼዶችን በመገንባትም ለባለሀብቶች አማራጭ መፍትሄዎች እየቀረቡ መሆኑን አስረድተዋል።
ከዚህም ባለፈ የፋይናንስ አቅርቦት እጥረትን ለመቅረፍ ከተለያዩ ባንኮች ጋር የጋራ ስራዎች መጀመራቸውን ጠቁመዋል።
አቶ ጳውሎስ እንዳብራሩት፣ ባለሀብቶች ወደ ቢሮዎች በአካል በመመላለስ የሚባክንባቸውን ጊዜና ጉልበት ለመቀነስ በቴክኖሎጂ የታገዘ የኦንላይን አገልግሎት ተዘርግቷል።
ይህም ባለሀብቶች ካሉበት ሆነው ጥያቄዎቻቸውን እንዲያቀርቡና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ፈጣን ምላሽ እንዲያገኙ የሚያስችል በመሆኑ፣ አዲስ አበባን ለኢንቨስትመንት ይበልጥ ተመራጭ ያደርጋታል በለዋል።
በበረከት ጌታቸው