AMN – መጋቢት 05/2018 ዓ.ም
ታላቁ የረመዳን ጾም ማጠናቀቂያ እና የዒድ-አልፈጥር በዓል መቃረቡን ተከትሎ፣ በመላው አዲስ አበባ የሚገኙ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የኤግዚቢሽንና የባዛር መርሃ ግብሮች መጀመራቸውን የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ ገለጹ።
ምክትል ከንቲባው እንደገለጹት፣ የባዛር ዝግጅቶቹ ለመላው የከተማዋ ነዋሪዎች አንፃራዊ ቅናሽ ባለው ዋጋ ምርቶች የሚቀርብብት ነው።
በዓላቱን ምክንያት በማድረግ በተለይ ለፍጆታ የሚሆኑ መሰረታዊ ምርቶች በቅናሽ ዋጋ እንዲቀርቡ ተደርጓል።
ባዛሮቹ ነዋሪዎች የበዓላት ፍጆታን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲሸምቱ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር አልመው የተዘጋጁ ሲሆን ፣ ከረመዳን ማጠናቀቂያ በኋላ የትንሳኤ በዓል ታሳቢ በማድረግም የምርቶች አቅርቦት ያለምንም መቋረጥ እንዲቀጥል ይደረጋል ።
ለዚህም የክፍለ ከተማ እና የወረዳ አመራሮች ምርቶች በስፋት ለህዝብ የሚቀርቡባቸውን ተጨማሪ ዕድሎች እንዲያመቻቹ አቶ ጃንጥራር አባይ ጥሪ አቅርበዋል።
ይህ ተግባር የነዋሪዎችን የዕለት ተዕለት ፍጆታ ለማቃለል የሚደረግ የዘወትር ስራ አካል መሆኑንም ገልጸዋል።
በበዓላት ወቅት የሚታየውን የገበያ ጫና ለመቀነስም የኤግዚቢሽን እና ባዛር መድረኮች ሚናቸው የላቀ ነው።
በበረከት ጌታቸው