AMN መጋቢት 5/2018 ዓ.ም
በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጥራት ያለው የጤና ትምህርት ይኖር ዘንድ ጤና ሚኒስቴር ከተቋማቱ ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን በምረቃ መርሃግብሩ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅድስ ዳባ ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የጥቁር አንበሳ ስሻላይዝድ ሆስፒታልን ጨምሮ በአምስት ትምህርት ቤቶች እና ሶስት የተለያዩ ግቢዎች ተደራጅቶ በመማር ማስተማር፣ በምርምርና በማህበረሰብ ጤና አገልግሎት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል፡፡
ኮሌጁ በተለያዩ የህክምና ዘርፎች ያሰለጠናቸውን 263 የህክምና ባለሙያዎች አስመርቋል፡፡

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅድስ ዳባ በሀገር አቀፍ ደረጃ የጤናውን ስርአት ለማዘመን፣የጤና አገልግሎቶችን ተደራሽነት ለማሳደግ እንዲሁም ፍትሐዊና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለመስጠት በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን አንስተዋል፡፡
በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጥራት ያለው የጤና ትምህርት ይኖር ዘንድ ጤና ሚኒስቴር ከተቋማቱ ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑንም ሚኒስትሯ አብራርተዋል፡፡
ተመራቂዎችም በሙያቸው የሚጋጥሟቸውን ችግሮች በመፍታት ማህበረሰቡን በታመኝነት እንዲያገለግሉም ዶክተር መቅድስ አሳስበዋል፡፡

አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሀገሪቱን የጤና ስርዓት በጥናትና ምርምር ለመደገፍና በቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት እንደእስካሁኑ ሁሉ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
እራሳቸውን በእውቀት በመገንባት ማህበረሰቡን በቅንነት ለማገልገል ቁርጠኛ መሆናቸውን ተመራቂዎች ተናግረዋል፡፡
ከተመራቂዎቹ ውስጥ 225ቱ በቅድመ ምረቃ መርሃ ግብር ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ሲሆን 16 በጥርስ ህክምና 22ቱ ደግሞ በአንስቴዥያ ሙያ መመረቃቸውን በምረቃ መርሃግብሩ ላይ ተገልጧል፡፡
በአልማዝ ሙሉጌታ