AMN መጋቢት 5/2018
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጋሞ ዞን በጋጮ ባባ ወረዳ በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች የተጀመረው የሰብዓዊና የዘላቂ መፍትሔ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ ባወጣው መግለጫ በጋሞ ዞን በጋጮ ባባ ወረዳ የካቲት 30 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ እስከ መጋቢት 1 ቀን 2018 ዓ.ም በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት በተከሰተው የመሬት መንሸራተት ናዳ እና የጐርፍ አደጋ የዜጎች ህይወት ማለፉን አመልክቷል።

ኮሚሽኑ በአደጋው ህይወታቸው ላለፉ ወገኖች የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን በመግለጽ ለተጎጂ ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን ተመኝቷል።
ከክልሉ መንግስት ጋር በመሆን የጀመረውን የሰብዓዊና የዘላቂ መፍትሔ ድጋፎችን ለማድረግና ለማስተባበር ብርቱ ጥረት እንደሚያደርግም ገልጿል።
በዘንድሮ በልግ ወቅት የሚከሰተው ዝናብ መደበኛና ከመደበኛ በላይ እንደሚሆን በሚቲዎሮሎጂ ትንበያ መሠረት የሚጠበቅ ሲሆን፣ ከመደበኛ በላይ በሚዘንብባቸው አካባቢዎች የጎርፍ፣ የመሬት መንሸራተት፣ የናዳ ጉዳትና ውድመት ሊያስከትል እንደሚችል ነው ያስታወቀው።
በተጋላጭነት በተለዩ አካባቢዎች የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎች ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉና የአደጋ ምልክቶች ሲታዩ በፍጥነት በዙሪያው ላሉ የመንግስት መዋቅሮች የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃ እንዲሰጥና ጉዳትና ውድመት የሚከላከሉ እርምጃዎች እንዲወስድ ኮሚሽኑ አሳስቧል።