ፊቼ ጫምባላላ አንድነትና አብሮነትን በመስበክ ለማህበራዊ ትስስር መጠናከር ጉልህ ሚና አለው-አፈ ጉባዔ አገኘው ተሻገር

You are currently viewing ፊቼ ጫምባላላ አንድነትና አብሮነትን በመስበክ ለማህበራዊ ትስስር መጠናከር ጉልህ ሚና አለው-አፈ ጉባዔ አገኘው ተሻገር

AMN መጋቢት 6/2018

ፊቼ ጫምባላላ አንድነትና አብሮነትን በመስበክ ለማህበራዊ ትስስር መጠናከር ጉልህ ሚና እንዳለው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘው ተሻገር ተናገሩ።

የሲዳማ ዘመን መለወጫ በዓል የሆነው ፊቼ ጫምባላላ የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አያንቱዎች፣ አባ ገዳዎች፣ ወጣቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በሀዋሳ ሶሬሳ ጉዱማሌ በደማቅ ስነ ስርዓት እየተከበረ ይገኛል።

በዓሉን የታደሙት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘው ተሻገር እንደተናገሩት ፊቼ ጫምባላላ ልዩ መልክና ልዩ ገጽታ ያለው ትልቅ ኢትዮጵያዊ በዓል ነው።

በዓሉ አብሮነትን፣ ሰላምን፣ ይቅርታን እያስተማረ ያለ የዘመን መሻገሪያ በዓል ነው ያሉት አፈ ጉባዔው፤ አንድነትንና አብሮነትን በመስበክ ለማህበራዊ ትስስር መጠናከር ጉልህ ሚና እንዳለውም ተናግረዋል።

የሲዳማ የአዲስ ዘመን ብስራት የሆነው ፊቼ ጫምባላላ በዓል ቂምና ቁርሾ ተሽሮ በሠላምና በይቅርታ አዲሱን ዘመን የሚቀበሉበት መሆኑን አንስተዋል።

የአንድነትና አብሮነት መተሳሰሪያ መሠረት የሆነው የፊቼ ጫምባላላ በዓል በዚህ መልኩ መከበሩ ህጻናትና ወጣቶች ባህላቸውን እንዲያውቁና ሳይበረዝ እንዲሸጋገር ምቹ መደላድል መፍጠሩን ገልጸዋል።

ሀገሪቱ ያላት ዘርፈ-ብዙ ጸጋዎችን በመጠቀም ብልጽግናችንን ለማሳለጥ እጅ ለእጅ ተያይዘን ተግተን መሥራት ይገባናል ብለዋል።

ጫምባላላን ጨምሮ በዩኔስኮ የተመዘገቡ ዕሴቶች የዲፕሎማሲያችን መሣሪያዎች ናቸው ያሉት አቶ አገኘሁ፥ እነዚህን እሴቶች መጠበቅና ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ ይገባል ብለዋል።

ምርጫ ለብሔራዊ አንድነትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የጎላ ድርሻ እንዳለው አንስተው፥ ዘንድሮ የሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

በአሁኑ ወቅት በዓሉ በቄጣላ ትዕይንት፣የፈረስ ጉግስና በሌሎች መርሃ ግብሮች እየደመቀ ይገኛል።

በበዓሉ ላይ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች፣ እንግዶችና የብሔረሰብ ተወካዮች መታደማቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review