አዲስ አበባን ያደመቁት የፈረንሳይ ቤላ የጎዳና ላይ ሥዕሎች

You are currently viewing አዲስ አበባን ያደመቁት የፈረንሳይ ቤላ የጎዳና ላይ ሥዕሎች

AMN – መጋቢት 6/2018 ዓ.ም.

ዛሬ አዲስ አበባን ለማድነቅ የግድ ሙዚየም መግባት አይጠበቅብዎትም፤ መንገዶቿ ራሳቸው ታሪክ መተረክ ጀምረዋል።

በኮሪደር ልማቱ አማካይነት በተለይም በፈረንሳይ ቤላ አካባቢ የሚገኙት ግዙፍ የሥዕል ሥራዎች የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ፣ ለወጣት ሰዓሊያን የሥራ ዕድልን፣ ለነዋሪው ደግሞ ታሪክ እያጋሩ ይገኛሉ።

ቀደም ሲል በቤታቸው ተወስነው ይሠሩ የነበሩ ወጣት ሠዓሊያን፣ አሁን በአደባባይ ችሎታቸውን እንዲያሳዩ የኮሪደር ልማቱ ሰፊ የፈጠራ አድማስ ከፍቶላቸዋል።

እነዚህ ግዙፍ የሥዕል ሥራዎች እንደ እንደስፋታቸው አይነት እስከ ሦስት ወር የሚፈጅ ጥረት የሚጠይቁ ሲሆን፣ ውጤታቸው ግን የከተማዋን ድባብ ሙሉ በሙሉ ቀይሮታል።

በግድግዳዎቹ ላይ የሚታዩት ሥዕሎች ዝም ብለው የሚታዩ ውበቶች ብቻ አይደሉም፣ ሀገራዊ ራዕይን የሚያንፀባርቁ እንጂ።

የኢትዮጵያንም የባሕር በር ባለቤትነት ተስፋ የሚያሳዩ ግዙፍ የመርከብ ሥዕሎች፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላኖች በጉልሕ ተስለውባቸዋል፤ በዚህም የጎዳና ላይ ሥዕሎቹ የሀገራችንን ማንነትና ታሪክ የሚዘክሩ ጥበባዊ ሥራዎች መሆን ችለዋል።

“ስለ ቀይ ባሕርና ስለ ወደብ ጉዳይ ለሕጻናትና ለአካባቢው ነዋሪዎች ትልቅ ትምህርት እየሰጠን ነው” ብለዋል ወጣት ሠዓሊያኑ። ወጣት ሴት ሰዓሊያንም በንቃት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በጎዳና ላይ ወጥቶ ሥዕል መሥራት የራሱ ጫና ቢኖረውም፣ ከአላፊ አግዳሚው የሚሰጠው አዎንታዊ አስተያየት ግን ብርታት እንደሆናቸው ገልጸዋል፡፡

የሥዕል ሥራው ለራሳቸው ገቢ ከመፍጠር ባለፈ ቤተሰቦቻቸውን መርዳት አስችሏቸዋል፤ እንዲሁም በሙያቸው ለሀገር ገጽታ ግንባታ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ረድቷቸዋል።

የፈረንሳይ ቤላ የወንዝ ዳርቻ ልማትና የሥዕል ሥራዎች አዲስ አበባን ወደ ሥነ-ጥበብ ከተማነት እያሸጋገሯት ነው።

እነዚህ ሥራዎች የከተማዋን ውበት ከመጨመር ባለፈ፣ የወጣቶችን የፈጠራ አቅም ለዓለም የሚያሳዩና ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ድልድዮች ሆነዋል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review