AMN-መጋቢት 6/2018 ዓ.ም
በቀጣይ የውድድር ዓመት የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ላይ የሚያሳትፈውን ደረጃ ለማግኘት እየጣረ የሚገኘው ማንችስተር ዩናይትድ በኦልድትራፎርድ አስቶንቪላን ያስተናግዳል።
ዩናይትድ ሩበን አሞሪምን አሰናብቶ ማይክል ካሪክን ከሾመ በኋላ በሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ በኒውካስትል መሸነፉ ይታወሳል።
የሌሎች ክለቦች ነጥብ መጣል ግን ከሦስተኛ ደረጃው አላወረደውም።
ከ29 ጨዋታ 51 ነጥብ ያለው ዩናይትድ የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ በጥብቅ የሚፈልገውን የቻምፒየንስ ሊግ ተሳትፎ ለማግኘት መንገድ ጠራጊ ይሆንለታል።
አስቶንቪላ በሊጉ ያለው ብቃት ጥሩ የሚባል አይደለም። የኡናይ ኤምሬይ ቡድን ከመጨረሻው ስድስት የሊግ ጨዋታው አንዱን ብቻ አሸንፏል።

ቪላ ወደ ኦልድትራፎርድ የሚያቀናው በዎልቭስ እና ቼልሲ በተከታታይ ከተሸነፈ በኋላ ነው።
በመጀመሪያው ዙር ዩናይትድን 2ለ1 ያሸነፈው አስቶንቪላ ከ71 ዓመታት በኋላ የደርሶ መልስ ድል ለማግኘት ይጥራል።
ይህን ለማድረግ ግን በትልቁ የሚቸገር ይመስላል። ምክንያቱም ቪላ ወደ ኦልድትራፎርድ አቅንቶ ካከናወናቸው 37 የመጨረሻ የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው ሁለቱን ብቻ ነው።
በዛሬው ጨዋታ በዩናይትድ በኩል ሜሰን ማውንት ወደ ስብስቡ ሲመለስ ፣ ሊሳንድሮ ማርቲኔዝ እና ማታያስ ደሊግት ግን ዝግጁ አይደሉም።
አስቶንቪላ ከጉዳቱ ያገገመው አምበሉ ጆን ማጊንን መልሶ ያገኛል።
ጨዋታው 11 ሰዓት ሲል የሚጀመር ይሆናል።
በተመሳሳይ ሰዓት ኖቲንግሃም ፎረስት ከ ፉልሃም እንዲሁም ክሪስታል ፓላስ ከ ሊድስ ዩናይትድ ይጫወታሉ።
በሸዋንግዛው ግርማ