AMN – መጋቢት 6/2018 ዓ.ም
በታሪክ ማህደር ውስጥ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረውና ለበርካታ ዜጎች አካል ጉዳት ምክንያት የሆነው የስጋ ደዌ በሽታ፣ ዛሬም ድረስ በብዙዎች ዘንድ እንደ አስፈሪ የጤና ስጋት ይታያል።
ይሁን እንጂ የሕክምና ሳይንስ ዕድገት፤ በሽታውን ሙሉ በሙሉ መዳን ወደሚችል የጤና እክል ቀይሮታል።
በአለርት ሆስፒታል የቆዳ ሕክምና ስፔሻሊስት ሀኪም የሆኑት ዶክተር ጽዮን ተስፋዬ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለፁት የስጋ ደዌ ማይክሮባክቲሪየም ሌፕሬ በተባለ ባክቴሪያ አማካኝነት የሚከሰት ቢሆንም፣ ቀድሞ በሕክምና ከተደረሰበት መዳን ይቻላል።
በሽታው በቆዳ ላይ በሚታዩ ነጣ ወይም ቀላ ያሉ ቀለሞች እንዲሁም በእጅ እና በእግር ላይ በሚከሰት የመደንዘዝ ስሜት ራሱን መግለጥ ይጀምራል።

ባክቴሪያው ወደ ሰውነት ከገባ በኋላ ምልክት ለማሳየት በአማካይ ከሦስት እስከ አራት ዓመታት ሊፈጅ እንደሚችል ዶ/ር ጽዮን ያብራራሉ።
ይህ ረጅም ጊዜ ደግሞ ታካሚው በሽታው እየጸና መሄዱን ሳያስተውል እንዲቆይ ሊያደርገው ይችላል።
ዶክተር ጽዮን እንደሚመክሩት፣ ማንኛውም ሰው በቆዳው ላይ ለውጥ ሲያይ ወይም የመደንዘዝ ስሜት ሲሰማው በፍጥነት ወደ ሕክምና ተቋም መሄድ ይኖርበታል።
ምክንያቱም ጉዳት ከደረሰ በኋላ የሚሰጥ ሕክምና የደረሰውን ጉዳት ወደ ነበረበት መመለስ ስለማይችል፣ ቁልፉ መፍትሄ ቀድሞ መታከም ነው።
ስለ በሽታው መተላለፊያ መንገድ በህዝቡ ዘንድ ያለው የተሳሳተ ግንዛቤ ሌላኛው ትልቅ ፈተና ነው። ብዙዎች በሽታው በዘር እንደሚተላለፍ ወይም በቆዳ ንክኪ ብቻ እንደሚዛመት ቢያምኑም፣ እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ነው።

በሽታው ከእናት ወደ ልጅም አይተላለፍም፤ ይልቁንም ባክቴሪያው በከፍተኛ ሁኔታ ካለበት ሰው ጋር ለረጅም ጊዜያት በአንድ ቤት ውስጥ በመኖር፣ አየርን በመጋራት የሚተላለፍ ነው።
በተለይም ሥር የሰደደ ድህነት፣ ንጹህ አየር በሌለውና ከብዙ ሰው ጋር ለረጅም ዘመን በጋራ መኖር እንዲሁም የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ለበሽታው ተጋላጭነትን የሚጨምሩ ዋና ዋና ምክንያቶች ናቸው።
የስጋ ደዌ በሽታ በኢትዮጵያ ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት የሚወስድ የነፃ ሕክምና አለው። ይህ ሕክምና የታካሚውን ጤና ሙሉ በሙሉ መመለስ የሚችል ቢሆንም፣ በሽታው የሚያስከትለው ማሕበራዊ መገለል ግን አሁንም ፈውስ ያሻል።
በሽታው በአጋጣሚ በሚፈጠር ንክኪ የማይተላለፍ በመሆኑ፣ በበሽታው የተጠቁ ሰዎችን ማግለል ተገቢ እንዳልሆነ ዶክተር ጽዮን ያሳስባሉ። ይልቁንም ማሕበረሰቡ ለታካሚዎች አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ እና ግንዛቤ በመፍጠር ከማሕበራዊ መገለል ሊታደጋቸው እንደሚገባ ሙያዊ ምክራቸውን ለግሰዋል ።
በበረከት ጌታቸው