በመዲናችን አዲስ አበባ ባሳለፍነው ሳምንት የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች ለጥበብ አፍቃሪያን ሲደርሱ ቆይተዋል። ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናትም መሰል መሰናዶዎች ይቀርባሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል የኪነ ጥበብ ፌስቲቫል፣ የስዕል አውደ ርዕይና የመጽሐፍት ምረቃ ይገኙበታል፡፡ ለመረጃ ይሆንዎት ዘንድ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል እንደሚከተለው አዘጋጅቷቸዋል፡፡
የኪነ ጥበብ ፌስቲቫል
17ኛው ከተማ አቀፍ የኪነ ጥበብ ፌስቲቫል ሳምንት ከዛሬ ጀምሮ እስከ መጋቢት 7 ቀን 2018 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ ለሦስት ተከታታይ ቀናት ይካሄዳል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ባህል እና ኪነ ጥበብ ቢሮ በየዓመቱ የሚያሰናዳው ይህ ፌስቲቫል ዘንድሮ “የጥበብ ስጦታ ለኢትዮጵያ ከፍታ!” በሚል መሪ ሃሳብ በመስቀል አደባባይ ይካሄዳል፡፡ ፌስቲቫሉ የከተማዋን የጥበብ መንፈስ የሚያድስ እንደሚሆንም ተገልጿል።
ላለፉት 16 ዓመታት በተከታታይ ሲካሄድ የቆየው ይህ ፌስቲቫል፣ በዚህ ዓመትም ለ17ኛ ጊዜ የሚካሄድ ነው። በመርሃ ግብሩ በ16 የተለያዩ የጥበብ ዘርፎች የሚካሄዱ ውድድሮች እንዲሁም የፈጠራ ሥራዎች የሚቀርቡበት በተለይም አውደ ርዕይ፣ ሲምፖዚየም (አውደ-ጥናት)፣ ጥበባዊ ውይይቶችና የልምድ ልውውጦች፣ ውድድሮች፣ ለዘርፉ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ የጥበብ ባለውለታዎች የሚዘከሩበት ልዩ መድረክ እና ሌሎችም እንደሚካሄዱበት ተገልጿል።
የፌስቲቫሉ ዋና ዋና ዓላማዎች በአዲስ አበባ ያሉ የኪነ-ጥበብ ተሰጥኦዎችን ለሕዝብ ማስተዋወቅ፣ በጀማሪ እና በባለሙያ (Professional) ጥበበኞች መካከል የልምድ ልውውጥ መፍጠር፣ አዳዲስ ባለተሰጥኦዎችን ማበረታታት፣ ዕውቅና መስጠት እና በኪነ-ጥበብ የበለፀገች ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ እንደሆነ ተገልጿል።
መጽሐፍት
“አክሊሉ” የተሰኘው ታሪካዊ ልብ ወለድ መጽሐፍ በዛሬው ዕለት ይመረቃል፡፡ መጋቢት 5 የጸሐፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ልደታቸው ሲሆን፤ “አክሊሉ” የሚል በህይወት ታሪካቸው ላይ የተመሰረተ ልብ ወለድ መጽሐፍም በዕለቱ ይመረቃል፡፡ የመጸሐፉ ደራሲ ሰላማዊት ታደሰ (ዶ/ር) ስትሆን ከቀኑ በ8፡00 ሰዓት ጀምሮ በብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት በሚገኘው የታሪክ አደራ አዳራሽ ዘጠነኛ ፎቅ እንደሚመረቅ ተገልጿል፡፡
የሐሳብና የመጽሐፍት መድረክ
በዛሬው ዕለት የሐሳብ እና መጽሐፍት መድረክ ይካሄዳል፡፡ የውይይት ርዕሱ “የዓለም መቀዛቀዝ ለኢትዮጵያ ተስፋ? የአምራች ኢንዱስትሪው ዕውነታ፣ ዕድሎችና፣ አቅጣጫ…” የሚል ነው፡፡ በጉዳዩ ላይ መነሻ ሐሳብ የሚያቀርቡት ብርሃኑ በሻህ (ዶ/ር) እና አማረ ማተቡ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ ውይይቱ ከቀኑ 8:00 ሰዓት ጀምሮ አራት ኪሎ ዋልያ አዳራሽ ኢክላስ ሕንጻ 4ኛ ፎቅ ይካሄዳል፡፡
የስዕል አውደ ርዕይ
“የፈጠራ ጉዞን ማስተጋባት” የተሰኘው የስዕል አውደ ርዕይ በእይታ ላይ ይገኛል። አውደ ርዕዩ የተከፈተው ባሳለፍነው ሐሙስ ሲሆን፣ የኢትዮዽያ የሴት ሰዓሊያን ማህበር የ17 ሰዓሊያን ሥራዎች ያቀረበበት ነው፡፡ ፈንድቃ የባህል ማዕከል እና ሀያት ሪጀንሲ ሆቴል በመተባበር ያዘጋጁት ይህ አውደ ርዕይ 24 ሰዓት ለተመልካች ክፍት የሆነና እስከ መጋቢት 21 ቀን 2018 ዓ.ም የሚቆይ ነው፡፡
በጊዜው አማረ