ፊቼ ጨምበላላ ከውበት ባሻገር በውስጡ በርካታ እሴቶች መያዙን መረጃዎች ያመላክታሉ
የሲዳማ የዘመን መለወጫ ተፈጥሮና ሰው በአንድ ድምፅ ለሰላም የሚዘምሩበት ረቂቅ ምስጢር ነው። ምክንያቱም ፊቼ ጨምበላላ በዓል ብቻ አይደለም፤ የነፍስ መታደሻ፣ የቂም መደምሰሻና የፍቅር መድረክ ነው። የጨረቃና የከዋክብት ውህደት የአዲሱን ዓመት ብርሃን ሲያበስሩ፣ የሰው ልጅ ልብም በይቅርታ ብርሃን ይሞላል።
በፊቼ ጨምበላላ ምድር ከጥላቻ ትላቀቃለች። ገንዘብ ያበደረ “ክፈለኝ” ብሎ ተበዳሪውን አይጠይቅም፡፡ አያስጨንቅም፡፡ ምክንያቱም በዚያች ዕለት ከገንዘብ ይልቅ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት ይገዝፋልና። የበደለ ካሳ ሳይጠየቅ፣ የገፋ ይቅርታ ሳይለምን፣ ሁሉም በነጻነት ወደ ፍቅር አደባባይ ይተምማሉ። ይህ እሴት የሲዳማ ሕዝብ ለሀገራችን እና ለዓለም የቸረው የሞራል ልዕልና ማሳያ ሲሆን፣ ሰላም በቃላት ሳይሆን በተግባር የሚተረጎምበት ሕያው ተምሳሌት ነው።
በፊቼ ጨምበላላ ዋዜማ፣ በሲዳማዎች ቤት ውስጥ የሚበራው መብራት የደስታ ብቻ ሳይሆን የጥበቃም ጭምር ነው። በዕለቱ ዛፍ አይቆረጥም፣ አዝመራ አይታጨድም፣ እንስሳትም አይታረድም። ተፈጥሮ ሙሉ ዕረፍት ታገኛለች። ትጠበቃለች፡፡ ይህ “ሕይወትን የማክበር” ጥበብ፣ በሰውና በፈጣሪ፣ በሰውና በተፈጥሮ መካከል ያለውን ጥብቅ ቁርኝት ያሳያል። በሲዳማዎች ምድር ቄጠላ ሲጨፈር፣ እግሮች ወደ ሰማይ ሲዘልሉ፣ ትከሻዎች በአንድነት ሲወዘወዙ፣ የሚሰማው የአንድነትና የፍቅር የልብ ትርታ ነው።
የባህል አጥኚው አቶ ብርሃኑ ሃንካራ በአንድ ወቅት በዓሉን አስመልክተው ለቢቢሲ እንደገለጹት “የፊቼ ጨምበላላ በዓል የሲዳማ ሕዝብ ማንነቱን ከተረዳበት ጊዜ አንስቶ ሲከበር የቆየ ነው’’ ይላሉ። ፊቼ ጨምበላላ በዓል የሚከበርበት ቋሚ ቀን የለውም። በአያንቱዎች ጥቆማ መሰረት በዓሉ የሚከበርበት ቀን ይቆረጣል። ከዚያም ለበዓሉ ሰፊ ዝግጅት ማድረግ ይጀመራል። ከዋዜማው አንስቶ በዓሉ መከበር ይጀምራል። ጎረቤት ተሰብስቦ ከእንሰት የሚዘጋጀውን ቦርሻሜ ተብሎ የሚጠራውን ምግብ ይመገባሉ። ለበዓሉ ከሚበሉ ባህላዊ ምግቦችና ከሚከናወኑ ጭፈራዎች በተጨማሪ የተለያዩ ባህላዊ ሁነቶችም ይካሄዳሉ። ቄጠላ፣ ኛፋሮና የመሳሰሉ ሙዚቃዎችም በበዓሉ ይከወናሉ።

የሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃጎ አገኘሁ በበኩላቸው የዘንድሮውን ፊቼ ጨምበላላ አስመልክተው በሰጡት መግለጫ በዓሉ ለሲዳማ ብሔር ከዘመን መለወጫነት ባሻገር ትልቅ ትርጉም ያለው የማንነቱ መገለጫ፤ የነፃነትና የፍቅር ማዕድ ሁሉም በጋራ የሚቋደስበት፤ የመንፃትና የመታደስ፤ አዲስ ተስፋ የሚሰነቅበት፣ በዳኤ ቡሹ እርስ በርስ ያላቸውን ፍቅር፣ አክብሮትና ደስታ የሚገልጹበት ነው ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በውስጡ ያሉ በርካታ እሴቶች በተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች የሚገለጹበት፣ እርቅ የሚፈፀምበትና ሀዘን የሚያበቃበት አልፎ ተርፎም በዓሉ ሲከበር አብሮነትን፣ አንድነትን፣ ፍቅርን፣ መረዳዳትን፣ መደማመጥን እንዲሁም መተባበርን የሚያጎሉ ድርጊቶች የሚፈጸሙበት ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ስለበዓሉ አከባበር በጥቂቱ
በቅድመ ፊቼ በዓሉ (ፊቼ) የሚውልበትን ቀን የመቁረጥ (ላላዋ)፣ ስለቀኑ ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር መምከር (ፋጆ)፣ በዓሉ የሚከበርበትን ቀን ሕዝብ በሚሰበሰቡበት ማወጅ (ላላዋ)፣ ጭሜሳዎች ስላላፈው ዓመት በሰውና በእንስሳ ስለተፈፀመ በደል ንስሃ እየገቡ የሚፆሙበት (ኡሱራ)፣ የፊቼ ቀን መቃረቡን ማብሰሪያ የጭሜሳዎች ቄጣላ (ሳፎተ ቄጣላ)፣ ወጣቶች ለበዓሉ የሚያስፈልጋቸውን ልብስና ቁሳቁስ ማሟላታቸውን እየገለፁ የሚከውኑት ቄጣላ (አድቻ ቄጣላ) እና ሁሉን አቀፍ ዕርቅ (አራራ) ይከናወናሉ፡፡
የፊቼ ዕለት ፊጣራ በመባል የሚታወቅ ሲሆን በዕለቱ ከ9:00 ወይም 10:00 ሰዓት ገደማ ደጅ ላይ በአግድም በእርጥብ እንጨት መሿለኪያ (ሁሉቃ) ተሠርቶ ሰውና የቤት እንስሳት በዚያ የሚሾልኩበት፣ ከአሮጌው ዓመት ወደ አዲሱ የመሸጋገር ተምሳሌት ይከናወናል። ከ12:00 ሰዓት ጀምሮ ደግሞ ቡሪሳሜ በሻፌታ ተዘጋጅቶ በጋራ ይበላል። ቡሪሳሜ በጋራ የመቋደስ ሥርዓት መጀመሪያ በጎሳ መሪ ወይም ጭሜሳ ቤት ይሆንና እንደየ እድሜ ቅደም ተከተል በዙር ሁሉም ቤት ይደርሳል።
በማግስቱ ቀኑ ጨምባላላ በመባል የሚታወቅ ሲሆን፤ ይህ ለልጆች፣ ለከብቶች፣ ለዱር እንስሳትና ለተፈጥሮ ልዩ ቀን ነው። በጨምባላላ ዕለት ልጆች ከቤት ቤት እየዞሩ “አይዴ ጨምባላላ!” እያሉ እናቶች “ኢሌ ኢሌ” ብለው ቡሪሳሜ እያበሏቸው ቀኑን ሲቦርቁ ይውላሉ። ከብቶችም ጥሩ ግጦሽ ወዳለበት የሚሰማሩበት፣ በአርጩሜ የማይመቱበት ዕለት ነው። የዱር እንስሳት የማይታደኑበት፣ የዛፍ ቅርንጫፍ የማይቆረጥበት ዕለትም ነው፡፡
ዩኔስኮ በይፋዊ ገጹ ላይ ባሰፈረው ጽሑፍ ፊቼ ጨምበላላ ከበዓልነት ባለፈም የእውቀት ሽግግር የሚደረግበት እለት ነው ይላል፡፡ ተቋሙ እ.ኤ.አ. በ2015 “Fichee-Chambalaalla, New Year festival of the Sidama people” በሚል ርዕስ ባሰፈረው ጽሑፍ ወላጆች በበዓሉ ላይ ወጉንና ባህሉን ለልጆቻቸው በምርቃት፣ በጭፈራ እና በቃል ያስተላልፋሉ። በተለይም ሴቶች የፀጉር አሰራርን እንዲሁም የቡሪሳሜ አዘገጃጀት እውቀትንና ክህሎትን ለሴት ልጆቻቸውና በአካባቢያቸው ለሚገኙ ልጃገረዶች ያስተምራሉ በማለት ገልጾታል።
ጨምበላላ እና ተዝናኖት
ፊቼ ጨምበላላ ቁምነገርና ተዝናኖት የሚሸመንበት እለት ነው፡፡ ከጨምባላላ ዕለት ቀጥሎ ሁሉም ጎሳ በየጉዱማሌው ስሜቱን በቄጣላ፣ በፋሮና ልጃገረዶች በሆሬ ክዋኔ ለሁለት ሳምታት የሚገልፁበት ጊዜ ይሆናል። የፊቼ ማሳረጊያ ዕለት ፊቺ ፉሎ ይባላል። በዚህ ዕለት ሁሉም ሰው ወደ ታላቁ ጉዱማሌ ይከትማል።
በፊቼ ጨምበላላ በዓል ማጠቃለያ ላይ የሚቀርበው ቄጠላ፣ የሲዳማ ሕዝብ ታሪኩን፣ እሴቱንና ወንድማማችነቱን የሚገልጽበት ደማቅ ባህላዊ የጭፈራ ሥነ-ሥርዓት ነው። ይህ ትዕይንት ወጣቶች፣ ጎልማሶችና አዛውንቶች በአንድነት በመሆን የአዲሱን ዓመት መባቻ የሚያበስሩበትና የሕዝቡን አንድነት የሚያሳዩበት ልዩ የጭፈራና እና የተዝናኖት መድረክ ነው።
በዚህ ባህላዊ ሙዚቃና ጭፈራ ወቅት፣ አገርና ዘመን በክብር ይወደሳሉ። ባለፈው ዓመት የተከናወኑ መልካም ተግባራት እየተዘከሩ፣ አዲሱ ዘመን የሰላምና የብልጽግና እንዲሆን በዜማ ይማጸናሉ። በተለይም የአገር ሽማግሌዎች ላበረከቱት የላቀ አስተዋጽኦ፣ ለሰጡት ጥበብና ለጠበቁት ሰላም በግጥም የሚወደሱበት፣ ታዋቂ ግለሰቦችም ለሕዝብ በሰሩት በጎ ሥራ የሚመረቁበት የክብር መገለጫ ነው።
ቄጠላ እንዲሁ ዝም ብሎ ጭፈራ ሳይሆን፣ የትውልድ ቅብብሎሽ የሚካሄድበት ታላቅ የባህል መድረክ ነው።፤ ተዝናኖት እና ቁም ነገርን በአንድ የያዘ፡፡ ተሳታፊዎቹ በዜማና በዝላይ የታጀበ እንቅስቃሴ እያደረጉ ወደ አደባባይ (ጉዱማሌ) በመትመም፣ የሲዳማን ሕዝብ ኩራትና ማንነት ለዓለም ያሳያሉ። ይህ ሥነ-ሥርዓት በዓሉ በታላቅ ድምቀት የሚጠናቀቅና በቀጣዩ ዓመትም በሰላም ለመገናኘት ቃል የሚገባባበት የማኅበረሰቡ የጋራ ድምፅ ነው።

ፊቼ ጨምበላላ የሀገርና የዓለም ሃብት
የፊቼ ጨምበላላ በዓል በዓለም አቀፉ የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) በማይዳሰሱ የዓለም ቅርሶች ዝርዝር ውስጥ መመዝገቡ፣ ለሲዳማ ሕዝብም ሆነ ለኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን ያስገኛል። ይህ እውቅና በዓሉን ከሀገር ውስጥ ባህላዊ ክዋኔ ወደ ዓለም አቀፍ የሰው ልጅ የጋራ ሀብትነት አሸጋግሮታል።
ማንኛውም ቅርስ በዩኔስኮ ሲመዘገብ የዓለም የቱሪስት መዳረሻ የመሆን ዕድሉ በከፍተኛ ደረጃ ይጨምራል። ፊቼ ጨምበላላም ለኢትዮጵያ፣ ለሀዋሳና ለሲዳማ ክልል ትልቅ የቱሪዝም በር ከፍቷል።
በየዓመቱ በዓሉ በሚከበርበት ወቅት ከውጭና ከሀገር ውስጥ የሚመጡ ቱሪስቶች ቁጥር እንዲጨምር አድርጓል። ይህ ደግሞ ለሆቴሎች፣ ለትራንስፖርት ዘርፉና ለባህላዊ ምርቶች አቅራቢዎች ትልቅ ገቢ ያስገኛል። በተጨማሪም የባህል አልባሳትን የሚያመርቱ፣ ባህላዊ ምግቦችን የሚያቀርቡና የቱሪስት አስጎብኚዎች ቁጥር እንዲጨምር በማድረግ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል።
የቢሮ ኃላፊው አቶ ጃጎ አገኘሁ የዘንድሮን በዓል ፊቼ ጫምባላላ ከሲዳማ እሴትነት አልፎ በዩኔስኮ የሰው ልጆች ወካይ የማይዳሰስ ባሕላዊ ቅርስ ዝርዝር መዝገብ ላይ መስፈሩን ተከትሎ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች የሚታደሙት ልዩ በዓል መሆኑን የገለጹትም ይህንኑ የሚያመላክት ነው።
በተጨማሪም የፊቼ ጨምበላላ እሴት የሆኑት ይቅርታ፣ እርቅ፣ ተፈጥሮን መንከባከብና ፍቅር ለኢትዮጵያ የሰላም ግንባታ ሂደት ትልቅ ትምህርት የሚሰጡ ናቸው። ዩኔስኮ ይህን የመሰለ የሰላም እሴት ያለው በዓል መመዝገቡ፣ ኢትዮጵያ የሰላም እሴቶች መፍለቂያ መሆኗን ለዓለም ያሳያል።
ፊቼ ጨምበላላ ኢትዮጵያ በርካታ የዩኔስኮ ቅርሶች ያሏት ሀገር መሆኗን በማጠናከር፣ የሀገሪቱን ገጽታ በጥሩ ሁኔታ ለመገንባት (Nation Branding) ይረዳል። ይህም ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተሰሚነትና ክብር ይጨምራል።
በአጠቃላይ፣ የፊቼ ጨምበላላ በዩኔስኮ መመዝገብ የሲዳማን ሕዝብ ማንነትና ባህል ለዓለም ከማስተዋወቁም በላይ፣ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚና የዲፕሎማሲ ስኬት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው። ይህ ቅርስ ተጠብቆ እንዲቆይ ማድረግ ደግሞ መንግሥትና ሕዝቡን ጨምሮ የባለድርሻ አካላት የጋራ ኃላፊነት ነው።
በጊዜው አማረ