ልጆች፤ ያላችሁን ተሰጥዖ ምን ያህል ታውቁታላችሁ?

You are currently viewing ልጆች፤ ያላችሁን ተሰጥዖ ምን ያህል ታውቁታላችሁ?

ልጆች እንዴት ናችሁ? ምን ዓይነት ተሰጥኦ አላችሁ? ይህን ቀድሞ ማወቅ ለምን እንደሚጠቅም ለማወቅ በጥበብ ዕድገት አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጎራ ብለናል፤ ተሰጥኦዋቸውን አውቀው ተግባር ላይ ያዋሉትን ልጆች ተሞክሮም ይዘንላችሁ ቀርበናል፤ መልካም ንባብ፡፡

ቴዎብስትያ ስንታየሁ እባላለሁ፤ 14 ዓመቴ ነው፡፡ ያለኝ ተሰጥኦ ሰርከስ ነው፡፡ ሰርከስ መሥራት ከጀመርኩ አራት ዓመት ሆኖኛል፡፡

 ይህን ያደረግኩት ጓደኞቼ ቀድመው በጀመሩት ሰርከስና ባሳዩት ትርኢት በመነሳሳት ነው፡፡ ከዚያም ለቤተሰቦቼ ነግሬ ስፖርቱን ሰለጠንኩ፡፡

የምሠራቸው የሰርከስ ዓይነቶች የሰውነት መተጣጠፍ፣ ላይራ (መንጠላጠል)፣ ስኬት፣ ቲሹ፣ በባለአንድ እግር ሳይክል ጎማ ላይ ትርኢት ማሳየት ናቸው፡፡ በዚህም ባለፈው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ከትምህርት ቤቱ ተመርጬ ትርኢት አቅርቤያለሁ። በዚህም በጣም ደስተኛ ነበርኩ፡፡ ያለኝን ተሰጥኦ ወድጄ እንድሠራ የተለያዩ ቁሳቁሶችን የሚያሟሉልኝ ቤተሰቦቼ እንዲሁም የሚያበረታቱኝ የቀለም እናትና አባቶቼ (መምህሮቼ) ናቸው፡፡ በዚህም ላመሰግናቸው እወዳለሁ፡፡

ስፖርቱን ስጀምር እንደ ጓደኞቼ ለመሥራት ነበር፡፡ አሁን ግን ፍላጎቴ እየጨመረ መጥቶ በሰርከሱ ዘርፍ የኢትዮጵያን ስም ማስጠራት እፈልጋለሁ።

ተሰጥዖን መከተል አላማን ለማሳካት ይጠቅማል፡፡ ይህ ተሰጥዖዬ በስራ  አለም ስኬታማ እንድሆን እንደሚያግዘኝ እርግጠኛ ነኝ፡፡  በአሁኑ ወቅት ሰውነቴም እንዲጠነክርና ቀልጣፋ እንድሆን ረድቶኛል፡፡

ተመስገን ብዙአየሁ እባላለሁ። የ6ኛ ክፍል ተማሪ ስሆን 13 ዓመቴ ነው፡፡ ሥዕል የመሳል ተሰጥኦ አለኝ። ተራራና ሐይቅን ጨምሮ የተለያዩ ሥዕሎችን እሥላለሁ፡፡ የሥዕል ተሰጥኦዬን ለማሻሻል ከትምህርት ሰዓት ውጭ ያለውን ጊዜና ቅዳሜና እሁድን እጠቀማለሁ፡፡ መምህሮቼም የንድፍ ሥራ እንዴት እንደሚሠራ ያሳዩኛል፤ የተለያዩ ሥዕሎችን ሥዬ እንዳሳያቸው በማድረግም ያበረታቱኛል። የስዕል ተሰጥኦዬ በአሁኑ ወቅት የእጅ ጽሑፌ የተስተካከለ እንዲሆን አድርጎኛል፡፡

ቤተልሔም ኃይልዬ እባላለሁ፡፡ የተለያዩ ሥነ ጽሑፎችን እጽፋለሁ፡፡ በጥበብ ዕድገት አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚከናወኑ ሳምንታዊ ክንውኖችን መረጃ በመውሰድ፣ አስፍቼና አቀነባብሬ በዜና መልክ አነባለሁ፡፡

ግጥሞችንና መነባንቦችን ጽፌ አቀርባለሁ። በትምህርት ቤታችን “የእኛው ለእኛው” በተሰኘ መርሐ ግብር ላይ መምህራንን እና ተማሪዎችን ቃለ መጠይቅ በማድረግና በመጻፍ በየሳምንቱ ዓርብ ጠዋት 2፡30 ሰዓት አቀርባለሁ፡፡ የቴአትርና የፊልም ጽሑፎችን እየጻፍኩ ለትምህርት ቤቱ እሰጣለሁ፡፡

የሥነ ጽሑፍ ፍላጎቴ የጀመረው ከሦስተኛ ክፍል ጀምሮ ነው፡፡ የከበደ ሚካኤልን ግጥሞች ሳነብ በጣም ደስ ይለኛል፡፡ “ቁጭ ብዬ ይህን ልጻፍ” ብዬ አቅጄ ጽፌ አላውቅም፤ የምጽፈው በድንገት ከምሰማው፣ ከማየው ወይም ከተከሰተው ነገር በመነሳት ነው። ይህ ፍላጎቴ እንዲጨምር ደግሞ ቤተሰቦቼ የተለያዩ የግጥም መጻሕፍትን እንዳነብብና የግጥም ርዕሶችን በመስጠት እንድጽፍ በማበረታታት ያግዙኛል። ይህን ተሰጥኦዬን በማሳደግ ወደፊት ጋዜጠኛ የመሆን ሕልም አለኝ፡፡

በፋንታነሽ ተፈራ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review