“ጉሮሮ ሲደርቅ፣ ሆድ ሲጮህ… እግር እንዴት ይሮጣል?” ለሚለው ጥያቄ ምላሹ ያለው ሜዳ ላይ ነው። ለብዙዎች ፆም የእረፍትና የዝግታ ወቅት ሲሆን፣ ለፕሮፌሽናል ስፖርተኞች ግን የሰውነትን ወሰን የሚፈትኑበት ጊዜ ነው። “ፆምና ስፖርት የማይገናኙ ናቸው” የሚለው አስተሳሰብ ዛሬ ታሪክ ሆኗል። ይልቁንም ፆም የስፖርተኛውን አእምሯዊ ጥንካሬ እንደሚጨምር ማረጋገጫ ከመስጠቱም በላይ በረመዳን ወቅት ሙስሊም ስፖርተኞች የሚያሳዩት ድንቅ ብቃት ለሌላ ምርምር ጭምር በር የከፈተ ሆኗል።
በዚህ አምድም የረመዳን ፆም በስፖርቱ ዓለም የፈጠረውን አዲስ ባህልና ህግ፣ ተጫዋቾች በረሃብና ጥማት ውስጥ ሆነው እንዴት አስደናቂ ብቃት እንደሚያሳዩና ሜዳ ላይ የሚፈጠሩ ልብ የሚነኩ ገጠመኞችን British Journal of Sports Medicine፣ ‘Fasting and Sport Performance’ በሚል ርዕስ ያወጣውን ጥናትና ሌሎች ምንጮችን ዋቢ አድረገን እንቃኛለን።
መነሻችንን የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ እናድርግ፤ በዚህ ሊግ ሙስሊም ተጫዋቾች ከንጋት እስከ ፀሐይ መጥለቅ ድረስ ያላቸውን መንፈሳዊ ግዴታ ከከባዱ የሜዳ ላይ ፉክክር ጋር አጣጥመው በመጓዝ ላይ ይገኛሉ። ሊጉ በዘንድሮው የውድድር ዘመን በ20ዎቹ ክለቦች ውስጥ ከ55 በላይ ሙስሊም ተጫዋቾችን የያዘ ሲሆን፣ እነዚህ ተጫዋቾች ጾማቸውን እየጾሙ ለቡድኖቻቸው ወሳኝ ግልጋሎት በመስጠት ላይ ናቸው።
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የፀሐይ መጥለቅን ተከትሎ ተጫዋቾች ውሃ በመጠጣት አልያም መለስተኛ ምግብ በመውሰድ እንዲያፈጥሩ አጭር ይፋዊ እረፍት እንዲሰጥ ይፈቅዳል፡፡ ፕሪሚየር ሊጉ ጾም ላይ ላሉ ተጫዋቾች ህይወትን ቀላል ለማድረግ “ተፈጥሯዊ እረፍት” የሚል ፕሮቶኮል ተግባራዊ ስለማድረጉም የስካይ ስፖርት መረጃ ያሳያል። ለ2025/26 የውድድር ዘመን፣ ዳኞችም ግልጽ የሆነ የጨዋታ እቅድ ተዘጋጅቶላቸዋል፡፡ ፀሐይ ስትጠልቅ ወይም ኢፍጣር ሲደርስ ተጫዋቾች ወደ ሜዳው ዳር በማምራት መጠጥ ወይም መለስትኛ ምግብ እንዲመገቡ ይደረጋል። ለዚህም የቡድን አንበሎች ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት ለዳኞቹ ቅድሚያ ማሳወቅ የሚጠበቅባቸው ሲሆን፣ ተጫዋቾችም ከአንድ ደቂቃ ባልበለጠ ጊዜ አፍጥረው ይመለሳሉ፡፡
ከአርሰናል እንደ ዊሊያም ሳሊባ፣ ከሊቨርፑል መሐመድ ሳላህ፣ ኢብራሂማ ኮናቴ እና ሁጎ ኤኬኬ እየፆሙ ይጫወታሉ። በማንቸስተር ሲቲ ራያን አይትኑሪ፣ ራያን ቼርኪ፣ ኦማር ማርሙሽ እና አብዱኮድር ኩሳኖቭን ጾመኛ ሆነው ሜዳ ይገባሉ፡፡ በማንቸስተር ዩናይትድ እንደዚሁ አማድ ዲያሎ፣ ኑሰይር መዝራዊ እና ግብ ጠባቂው አልታይ ባይንድይር የሚጾሙ ተጫዋቾች ናቸው፡፡
የቀድሞዎቹ አሰልጣኞች ፆመኛ ተጫዋቾችን ‘አትጹሙ’ ብለው ያስገድዱ ነበር። አሁን ላይ ግን እንደ ቀድሞ የሊቨርፑል የርገን ክሎፕ ያሉ ታዋቂ አሰልጣኞች ለተጫዋቾቻቸው ያላቸውን ክብር በተግባር አሳይተዋል፡፡ የክለቡ ድረ ገጽ መረጃ እንደሚያሳየው ክሎፕ ሊቨርፑል በነበሩበት ወቅት መሐመድ ሳላህና ሳዲዮ ማኔ ፆመው እንዲጫወቱ ክለቡ ልዩ የምግብ ባለሙያና የጸሎት ቦታ በማዘጋጀት ያደረገው ድጋፍ ለሌሎች ክለቦች አርአያ ሆኗል። ይህ ‘የብዝሃነት ውበት’ ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል።
በ2025 የውድድር ዘመን በጀርመን ቡንደስሊጋ የተከሰተውን እናስታውስ። ዋናው ዳኛ ማቲያስ ጆለንቤክ ጨዋታውን በድንገት አቆሙ። ተጫዋቾችና ደጋፊዎች ግራ ተጋብተው ሳለ፣ የሜይንዝ ተከላካይ ሙሳ ኒያካቴ ወደ ሜዳው ዳር ሮጦ ጥቂት ውሃ ጠጣ። ዳኛው ሆን ብሎ ጨዋታውን ያቆመው ለተጫዋቹ ፆም መፍቻ ሰዓት ደርሶ ስለነበር ነው። ኒያካቴ ውሃውን ጠጥቶ ሲመለስ ለዳኛው የሰጠው ‘አመሰግናለሁ’ የሚል እጅ መጨባበጥ፣ በስፖርቱ ዓለም ውስጥ ካሉ እጅግ ሰውኛና ልብ የሚነኩ ትዕይንቶች አንዱ ሆኖ ተመዝግቧል።
ይህ ትዕይንት በአሁኑ ወቅት በአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች የተለመደ ‘አስገራሚ ገጠመኝ’ ሆኗል። ከአስር ዓመታት በፊት አንድ ተጫዋች ፆመኛ ሆኖ ሜዳ ውስጥ ቢወድቅ ‘ለምን ፆምክ?’ የሚል ወቀሳ ይቀርብበት ነበር። ዛሬ ግን ታሪኩ ተቀይሯል። የሊቨርፑሉ መሐመድ ሳላህ በሻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ዋዜማ ላይ በፆም ሆዱ ልምምድ ሲሰራ ወይም ካሪም ቤንዜማ ቀኑን ሙሉ ሳይበላና ሳይጠጣ ምሽት ላይ በቼልሲ መረብ ላይ ሶስት ግቦችን ሲያዘንብ ስናይ፣ የሰው ልጅ መንፈሳዊ ጥንካሬ ከአካላዊ ውስንነት በላይ መሆኑን እንረዳለን።
የቀድሞ የሪያል ማድሪድ ኮከብ ካሪም ቤንዜማ በረመዳን ወቅት የሚያሳየው ብቃት ብዙዎችን ያስገርማል። አንድ ጊዜ በሻምፒዮንስ ሊግ ከቼልሲ ጋር ለሚደረግ ወሳኝ ጨዋታ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት ነበር ፆሙን የፈታው። “ሳይበላ እንዴት ይጫወታል?” ተብሎ ሲሰጋ፣ ቤንዜማ በዚያ ምሽት ሶስት ግቦችን በማስቆጠር ዓለምን አስገረመ። ከጨዋታው በኋላ “ፆም የበለጠ ትኩረት እንድሰጥና መንፈሴ እንዲጠነክር ያደርገኛል” ሲል መናገሩ፣ የስፖርት ሳይንቲስቶች ስለ ምግብና ጉልበት ያላቸውን ቀመር ደግመው እንዲፈትሹ አድርጓቸዋል።
በቱርክዬ ሊግ ጨዋታ ላይ ደግሞ ሌላ የሚደንቅ ክስተት ታይቷል። ጨዋታው እየተካሄደ እያለ የመግሪብ አዛን ተሰማ። በዚያ ቅጽበት አንዱ ተጫዋች ቆስሎ ሜዳ ላይ ወደቀ። ቡድኑ የሕክምና እርዳታ ለማግኘት በሚመስል መልኩ ተሰበሰበ። ነገር ግን ካሜራዎች ቀረብ ብለው ሲያሳዩ፣ ሁሉም ተጫዋቾች በኪሳቸው ይዘውት የነበረውን ቴምር እያወጡ ፆማቸውን ሲፈቱ ታዩ። ያ ጉዳት ተጫዋቾቹ ፆማቸውን እንዲፈቱ የተቀነባበረ ብልህ ዘዴ ነበር።
የዓለም ስፖርት አስተዳዳሪዎች ለፆመኞች ያላቸው አመለካከት ከመቻቻል አልፎ ወደ ደንብ ተቀይሯል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የወጡ አስገራሚ ህጎች አሉ። በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ እና በጀርመን ቡንደስሊጋ፣ ጨዋታው በሚካሄድበት ወቅት ፀሐይ የምትጠልቅ ከሆነ፣ ዳኞች ጨዋታውን ለጥቂት ደቂቃዎች እንዲያቆሙ በይፋ ተፈቅዶላቸዋል። ይህ ህግ ተጫዋቾች ሜዳው ዳር ቆመው ፆማቸውን እንዲፈቱ እድል ይሰጣል። አንዳንድ የአውሮፓ ክለቦችም ፆመኛ ተጫዋቾች ካሏቸው የቡድን ልምምዱን ወደ ጠዋት በጣም ቀደም ብሎ ወይም ወደ ምሽት ያዛውራሉ።
የሆላንዱ ፌይኖርድ እግር ኳስ ቡድን አሰልጣኝ ሩብን ቫን ፐርሲ በክለቡ ውስጥ ለሚገኙ ፆመኛ ተጫዋቾች ድጋፍ የሚሆን አዲስ አሰራር ይፋ ያደረገውም ከሰሞኑን ነበር። አሰልጣኙ ተጫዋቾቹ ኃይማኖታዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ ለማገዝ የልምምድ ሰዓት እና አይነት ላይ ማስተካከያ ማድረጉን ገልጿል። ፆመኛ ተጫዋቾች የሌሊቱን የዒባዳ እና የስሁር ሰዓት ታሳቢ በማድረግ፣ ጠዋት ወደ ልምምድ ሜዳ ዘግይተው እንዲመጡ ተፈቅዶላቸዋል። እንደዚሁም የፆመኞቹ የልምምድ ጫና እና አይነት ከሌሎች ተጫዋቾች የተለየ እንዲሆን ተደርጓል። ይህም ጉልበታቸውን በአግባቡ እንዲቆጥቡ ይረዳቸዋል ነው የተባለው። ቫን ፐርሲ “ቀኑን ሙሉ ሳይመገቡ መዋል ቀላል አይደለም” በማለት የተጫዋቾቹን ጥንካሬ አድንቆ፣ ክለቡ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጧል። ይህ ውሳኔ ቫን ፐርሲ ለተጫዋቾቹ ስነ-ልቦናዊ እና አካላዊ ብቃት ያለውን ጥንቃቄ የሚያሳይ እንደሆነ ስፖርታዊ ተንታኞች እየገለጹት ይገኛሉ።
በእርግጥ አንድ ስፖርተኛ ሳይበላና ሳይጠጣ 90 ደቂቃ ሙሉ ሜዳ ላይ መሮጥ የሚችለው በዘፈቀደ ሳይሆን በከፍተኛ የሳይንስ ጥናት ታግዞ ነው። የዘመኑ ስፖርት ሜዲስን ፆመኛ ተጫዋቾች ድካም እንዳይሰማቸው የሚያደርጉባቸው የተለያዩ መንገዶችንም እንደሚጠቀሙ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ጾም ለስፖርተኞች በአግባቡ ከተመገቡና የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ካስተካከሉ የጤና ጠቀሜታ እንዳለውም በBritish Journal of Sports Medicine ‘Fasting and Sport Performance’ ጥናታዊ ጽሁፍ ላይ ሰፍሯል። በጾም ወቅት የፕሮቲን፣ የካርቦሃይድሬት እና የፈሳሽ (ውሃ) ፍላጎትን በደንብ ማሟላት፣ የሥልጠና መጠኑን መቀነስ እና በቂ ዕረፍት ማድረግ የጡንቻ ጥንካሬን ለመጠበቅና የጉልበት ማጣትን ለመቀነስ ወሳኝ ነው። አሁን ላይ ትልልቅ ክለቦች የተጫዋቾችን መንፈሳዊ ፍላጎት የሚያውቁና ከአመጋገብ ባለሙያዎች ጋር በመቀናጀት የሚሰሩ አማካሪዎችን መቅጠር ጀምረዋል።
ፆምና ስፖርት ሲነሳ በአብዛኛው ትኩረቱ እግር ኳስ ላይ ቢሆንም፣ በሌሎች ስፖርቶች (በተለይ ከፍተኛ ጉልበት በሚጠይቁት) ውስጥ ያሉ ስፖርተኞች የሚያሳዩት ጽናት ይበልጥ አስገራሚ ነው። በአሜሪካ የቅርጫት ኳስ ሊግ (NBA) ውስጥ የሚታወቀው ካይሪ ኢርቪንግ፣ በረመዳን ወቅት ጨዋታዎች ሲኖሩት ፆመኛ ሆኖ ይገባል። በቅርጫት ኳስ ውስጥ ተጫዋቾች በየደቂቃው ወደ ላይና ወደ ታች ይሮጣሉ፤ ይህም ከፍተኛ የውሃ ጥም ያስከትላል።
በአንድ ወቅት ኢርቪንግ ፆመኛ ሆኖ 34 ነጥቦችን ያስቆጠረበት ጨዋታ ነበር። ከጨዋታው በኋላ በሰጠው ቃለ-መጠይቅ “ሰውነቴ ቢደክምም፣ መንፈሴ ግን በብርታት ተሞልቷል፤ ፆም ለእኔ እንደ ነዳጅ ነው” በማለት የገለጸው የብዙዎችን ቀልብ ስቧል። አሁን ላይ የNBA ቡድኖች ለፆመኛ ተጫዋቾቻቸው የቪታሚንና የፈሳሽ መጠንን የሚለኩ ልዩ ዲጂታል ሰዓቶችን (Wearable Tech) በመጠቀም ጤንነታቸውን ይከታተላሉ።
በቦክስ ስፖርት ውስጥ ፆም ትልቅ ፈተና ነው። ምክንያቱም ተጫዋቾች ለውድድር የሚመጥን ክብደት መጠበቅ አለባቸው። ታዋቂው ቦክሰኛ አሚር ካን በረመዳን ወቅት የልምምድ ሰዓቱን ሙሉ በሙሉ ወደ ለሊት በመቀየር ይታወቃል። እንደ ቤላል መሐመድ ያሉ የዩኤፍሲ (UFC) ተዋጊዎች በፆም ወቅት አፋቸው እንዳይደርቅ የሚጠቀሙት ብልሃት አፍን በውሃ መጉመጥመጥና መትፋት ብቻ ነው። ይህ በራሱ ትልቅ የሥነ-ልቦና ጽናት ይጠይቃል።
የአትሌቲክስ ስፖር እንደዚሁ ፈተናው ይበልጥ ይከብዳል። እ.ኤ.አ በ2012 የለንደን ኦሎምፒክ ከረመዳን ጋር ተገጣጥሞ ነበር። በወቅቱ ከ3 ሺህ በላይ ሙስሊም ስፖርተኞች ተሳትፈዋል። ብዙዎቹ ፆመው የተወዳደሩ ሲሆን፣ ሳይንቲስቶች ባደረጉት ጥናት ፆመኛ መሆናቸው በውጤታቸው ላይ ምንም አይነት አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳላመጣና አንዳንዶቹም የግል ምርጥ ሰዓታቸውን እንዳሻሻሉ ተመዝግቧል።
በሳህሉ ብርሃኑ