AMN-መጋቢት 7/2018 ዓ.ም
ማንችስተር ዩናይትድ ትናንት ምሽት አስቶንቪላን 3ለ1 አሸንፎ ወሳኝ ሦስት ነጥብ ሲያሳካ ቡርኖ ፈርናንዴዝ እንደተለመደው ጥሩ ብቃቱን አሳይቷል።
ፖርቹጋላዊው አማካይ ቀያይ ሰይጣናቱ ካስቆጠሯቸው ሦስት ግቦች ሁለቱን አመቻችቶ አቀብሏል።
በውድድር ዓመቱ በፕሪምየር ሊጉ የቡድን አጋሮቹ 16 ግቦችን እንዲያስቆጥሩ ረድቷል።
ይህም በማንችስተር ዩናይትድ ታሪክ በአንድ የውድድር ዓመት ከፍተኛ ግብ የሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ያቀበለ ቀዳሚው ተጫዋች አድርጎታል።
ከዚህ ቀደም ዴቪድ ቤካም 15 ግብ የሆኑ ኳሶችን በማቀበል የታሪኩ ባለቤት ነበር።
ፈርናንዴዝ በፕሪምየር ሊጉም አዲስ ታሪክ ለማፃፍ በቀሩት ስምንት ጨዋታዎች አምስት ግብ የሚሆኑ ኳሶችን ማቀበል ብቻ በቂው ነው።
አሁን ላይ ቴሪ ኦንሪ እና ኬቨን ደብሩየና በተለያየ ጊዜ 20 ግብ የሆኑ ኳሶችን በማቀበል ቀዳሚነቱን ይዘዋል።
ከአስቶንቪላው ጨዋታ በኋላ በዩናይትድ አዲስ ታሪክ ስለመስራቱ ሲጠየቅ “ታሪክ መስራቴ ሳይሆን ቡድኔን በመርዳቴ ደስተኛ ነኝ። ያገኘሁት ትልቅ ክብር እንደሆነ አውቃለሁ። ነገር ግን ከእኔ ይልቅ ቡድኔ ከፍ ሲል ማየት ነው የምፈልገው።” ብሏል።
በዩናይትድ ቆይታው በአጠቃላይ 318 ጨዋታ ያደረገው ቡርኖ ፈርናንዴዝ በ205 ግቦች ላይ ተሳትፎ አድርጓል ፤ 105ቱን በራሱ በማስመዝገብ ፣ 100ውን ደግሞ አመቻችቶ በማቀበል።
በሸዋንግዛው ግርማ