AMM – መጋቢት 7/2018 ዓ.ም
ባለፉት ዓመታት የተተገበረው ሀገራዊ የኢኮኖሚ ሪፎርም ኢትዮጵያን በአፍሪካ ግዙፍ ኢኮኖሚ ካላቸው ሀገራት ተርታ ማሰለፉን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዶ/ር ካሳሁን ጎፌ ገለጹ። ሚኒስትሩ ይህንን ያመለከቱት በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ትብብር “ኢትዮጵያ አዲሲቷ የኢንቨስትመንት መዳረሻ” በሚል መሪ ቃል በተዘጋጀ የፓናል ውይይት ላይ ነው።
በኢንቨስትመንት ዙሪያ ትኩረቱን አድርጎ እየተካሄደ በሚገኘው የፓናል ውይይት ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዶ/ር ካሳሁን ጎፌ፤ ሀገሪቱ የጀመረችው ኢኮኖሚያዊ ሪፎርም ተጨባጭና አበረታች ውጤቶችን እያስመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል።
ሪፎርሙ በተለይም የዋጋ ግሽበትን በመቆጣጠር እና የኢንቨስትመንት ምህዳሩን ይበልጥ ምቹ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ሚኒስትሩ ጠቁመዋል። ይህም ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ ካሉ ግዙፍ የኢኮኖሚ ኃይሎች መካከል አንዷ እንድትሆን አስችሏታል ብለዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም፣ ኢትዮጵያ እያቀረበችው ያለው የባህር በር ጥያቄ የፍትሃዊነት ጉዳይ መሆኑንና ይህም የሀገሪቱን የኢንቨስትመንት ተመራጭነት ይበልጥ ከፍ የሚያደርግ መሆኑን አስገንዝበዋል። “የተጀመረው ሪፎርም እንዳይቀለበስ ሆኖ እየተተገበረ ይገኛል” ሲሉም የለውጥ ሂደቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ በበኩላቸው፤ እንዲህ ያሉ መድረኮች ኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ያላትን እምቅ አቅም ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማስተዋወቅ ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸው ገልጸዋል።
በሀብታሙ ሙለታ