AMN መጋቢት 8/2018 ዓ.ም
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልእክት የሎጂስቲክስ ሉዓላዊነታችንን በራስ አቅም የማረጋገጥ አዲስ ምዕራፍ ላይ ነን ብለዋል፡፡
ዛሬ በእንዶዴ ደረቅ ወደብ ማስፋፊያ እና በኤኤምጂ (AMG) – እንዶዴ የባቡር መሥመር ፕሮጀክቶች ላይ ያደረግነው ምልከታ፤ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሪፎርም በጠንካራ መሠረት ላይ እየቆመ ለመሆኑ በተግባር ያረጋገጠ ነው።
የኤኤምጂ – እንዶዴ የባቡር መሥመር በሀገር በቀል የግል ኩባንያ ፋይናንስ የተደረገ የመጀመሪያው የባቡር መሠረተ ልማት ነው። ይሄም የግል ዘርፉ ለሀገር ግንባታ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል። በልዩ ትኩረት ከተያዘለት ጊዜ ቀድሞ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑም “ዐቅዶ መጀመር፣ ጀምሮ መፈጸም” የሚለውን መርሐችንን ያጸና ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ይህ የሦስት ኪሎ ሜትር ባቡር መሥመር በገላን ኢንዱስትሪ ዞን የሚመረቱ ምርቶችን ቡናን ጨምሮ በቀጥታ ከባቡር መሥመሩ ጋር በማገናኘት፣ ምርቶች በፍጥነትና በተወዳዳሪ ዋጋ ለዓለም ገበያ እንዲቀርቡ ያስችላል።
የእንዶዴ ደረቅ ወደብ ማስፋፊያ የኮንቴነር ማከማቻ ዐቅምን በ5 እጥፍ ሲያሳድግ፤ የጭነት የማውረድና የመጫን መጫኛ ጊዜን ከ10 ሰዓት ወደ ሁለት ሰዓት ዝቅ በማድረግ የንግድ ሥርዓታችንን ያዘምናል፤ ፈጣን የሎጂስቲክስ አገልግሎትን ይፈጥራል።
እነዚህ በራስ ዐቅም የሚገነቡ መሠረተ ልማቶች የሎጂስቲክስ ተወዳዳሪነታችንን ከማሻሻል ባለፈ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነታችንን ያጸናሉ። ኢትዮጵያን የአፍሪካ የንግድና የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ የምናደርገውን ጉዞ አጠናክረን እንቀጥላለን! ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡