የኢትዮጵያን የትራንስፖርት ዘርፍ ወደ ኤሌክትሪክና የተፈጥሮ ጋዝ የማሸጋገር እና የነዳጅ ቁጠባ ሀገራዊ ጥሪ

You are currently viewing የኢትዮጵያን የትራንስፖርት ዘርፍ ወደ ኤሌክትሪክና የተፈጥሮ ጋዝ የማሸጋገር እና የነዳጅ ቁጠባ ሀገራዊ ጥሪ

AMN መጋቢት 8/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ቀዳሚ መሪነት፤ ሀገርን ከውጭ ጥገኝነት ለማላቀቅ የራስን የተፈጥሮ ጸጋ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችሉ ስትራቴጂካዊ እርምጃዎችን ስትወስድ ቆይታለች።

ከእነዚህም መካከል የትራንስፖርት ዘርፉን ወደ ኤሌክትሪክ ኃይል የማሸጋገር (Transport Electrification) መርሐ-ግብር አንዱ እና ዋነኛው ስኬት ነው።

በአሁኑ ወቅት በመካከለኛው ምሥራቅ በተከሰተው ጦርነት ምክንያት የዓለም የነዳጅ ገበያ ለከፍተኛ መናወጥ እና አደጋ በተጋለጠበት ወቅት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአራት ዓመታት በፊት የነዳጅ እና የሌላ ማበረታቻ እንዲያገኙ ያደረጉት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ፖሊሲ፤ ዛሬ ላይ ሀገርን ከፈተና የሚታደግ ብልህ እና አርቆ አሳቢ ውሳኔ መሆኑ በተግባር ተረጋግጧል።

በስንዴ በራስ አቅም በመተካት የተመዘገበው ታሪካዊ ድል፤ ዛሬ በነዳጅ ዘርፍም እንዲደገም መንግሥት በቁርጠኝነት እየሠራ ይገኛል።

በመሆኑም፣ ወቅታዊውን ዓለም አቀፍ ጫና ለመቋቋም እና የሀገርን ኢኮኖሚ በዘላቂነት ለመታደግ የሚከተሉት አራት ዋና ዋና ነጥቦች በሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ በመንግሥት እና በግል ተቋማት ዘንድ ተግባራዊ እንዲሆኑ ጥሪ ቀርቧል፦

1. የቴክኖሎጂ ሽግግርና የኃይል አጠቃቀም

• የኤሌክትሪክ መኪናዎች ባህል፦ የኤሌክትሪክ መኪናዎችን መጠቀም እንደ ሀገራዊ ባህል በትኩረት ማዳበር።

• ከነዳጅ ወደ ኤሌክትሪክ ሽግግር፦ በነዳጅ እና በኤሌክትሪክ የሚሠሩ (Plug-in Hybrid) ተሽከርካሪዎች ነዳጅን በመተው የኤሌክትሪክ ኃይልን ብቻ እንዲጠቀሙ ማስቻል፤ እንዲሁም በነዳጅ የሚሠሩትን ወደ ኤሌክትሪክ እና ተፈጥሮ ጋዝ የመቀየር ሥራን ማጠናከር።

• ከባድ ተሽከርካሪዎች፦ እስከ 20 ቶን የሚጭኑ የጭነት ተሽከርካሪዎች ወደ ኤሌክትሪክ፤ ከ20 ቶን በላይ የሆኑት ደግሞ ወደ ተፈጥሮ ጋዝ እና ኤሌክትሪክ እንዲቀየሩ መንግሥት እና የግል ዘርፍ በቅንጅት እንዲሠሩ ማድረግ።

2. የመንግሥት እና የሕዝብ ትራንስፖርት ሚና

• የመንግሥት ተሽከርካሪዎች፦ በክልል እና በፌዴራል ደረጃ ያሉ ሁሉም የመንግሥት እና የፕሮጀክት ተሽከርካሪዎች ሙሉ በሙሉ ወደ ኤሌክትሪክ እንዲዘወሩ በማድረግ የተጀመረውን ሀገራዊ ዕቅድ ወደ ሙሉ ትግበራ ማሸጋገር።

• የሕዝብ ትራንስፖርት፦ ባቡሮችን፣ ባሶችን እና ሌሎች የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎቶችን በስፋት እና በአግባቡ መጠቀም፤ አገልግሎቱም በወጣለት ታሪፍ እና መርሐ-ግብር ያለ መቆራረጥ እንዲሰጥ በትብብር መሥራት።

3. የአጠቃቀም እና የአነዳድ ባህል ለውጥ (Eco-Driving)

• የግል ተሽከርካሪዎች ገደብ፦ ከአንድ ቤት ውስጥ ብዙ መኪናዎችን ይዞ መንገድ ከመውጣት ይልቅ፤ በጋራ የመጠቀም ልምድን ማዳበርና ተግባራዊ ማድረግ።

• አረንጓዴ ጉዞዎች፦ በከተማ ውስጥ የሚደረጉ አጫጭር ጉዞዎችን በእግርና በብስክሌት የማድረግ ባህልን ማሳደግ።

• የአነዳድ ክህሎት (Eco-driving)፦ ነዳጅንና የካርቦን ልቀትን የሚቀንሱ፣ ከሞኖፖሊነት የጸዳ የ”Eco-driving” የአነዳድ ስልጠና ለተሽከርካሪ አሽከርካሪዎች መስጠትና ልምዱን ማዳበር።

4. የጥራት ቁጥጥር እና የአካባቢ ጥበቃ

• ጥገናና መለዋወጫ፦ ወቅታዊ የመኪና ጥገናን ማጠናከርና ኦሪጅናል መለዋወጫዎችን መጠቀም።

• የጭስ ልኬትና ስታንዳርድ፦ የጭስ ልኬት መመሪያን በተሟላ ሁኔታ (100%) መተግበርና ሁሉም ተሽከርካሪዎች በኢትዮጵያ ስታንዳርድ የጸደቁ የነዳጅና ጭስ መቆጣጠሪያ ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀሙ ማድረግ።

ማጠቃለያ

ይህ የትብብር ጥሪ የሀገርን የውጭ ምንዛሬ ለማዳን፣ የአካባቢ ብክለትን ለመቀነስና ዜጎች በዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ መዋዠቅ እንዳይጎዱ ለማድረግ የታለመ ነው። የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩን የአመራር ራዕይ ይበልጥ ለማሳካትና ሀገርን ከጥገኝነት ለማላቀቅ ሁላችንም በኃላፊነት ስሜትና በቁርጠኝነት እንድንነሳ እናሳስባለን።

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review