AMN-መጋቢት 8/2018 ዓ.ም
የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ዙር የመልስ ጨዋታዎች ዛሬ ይጀምራሉ።
በዛሬው ዕለት አራት ጨዋታዎች ሲከናወኑ ማንችስተር ሲቲ በሜዳው ኢትሃድ ሪያል ማድሪድን የሚያስተናግድበት በጉጉት ይጠበቃል።
ሁለቱ ክለቦች ከሳምንት በፊት በሳንቲያጎ ቤርናቢዩ ያከናወኑት ጨዋታ በሪያል ማድሪድ 3ለ0 አሸናፊነት መጠናቀቁ ይታወሳል።
ሲቲ ከባድ ቢመስልም ውጤቱን ለመቀልበስ ይፋለማል። ታሪክ ግን ከማንችስተር ሲቲ ጎን አይደለም።
ሪያል ማድሪድ በጥሎ ማለፍ የመጀመሪያው ጨዋታ ሦስት እና ከዚያ በላይ ግቦችን አስቆጥሮ ባሸነፈባቸው 35 የአውሮፓ ውድድር ጨዋታዎች በሁሉም ወደ ቀጣዩ ዙር አልፏል።
ፔፕ ጋርዲዮላም ከ2014/15 የውድድር ዓመት በኋላ በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ጥሎ ማለፍ የመጀመሪያ ጨዋታውን ተሸንፎ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፎ አያውቅም።
በሊጉ ተከታታይ ነጥቦችን ጥሎ ከዋንጫው ፉክክር እየራቀ የሚገኘው ማንችስተር ሲቲ ከማድሪድ ጋር ባደረጋቸው የመጨረሻ አራት የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታዎች በሦስቱ ተሸንፏል።
ከተጫዋቾች ጋር በተያያዘ ሲቲ አዲስ የጉዳት ዜና የለበትም።
ሪያል ማድሪድ ኪሊያን ምባፔ እና ጁድ ቤሊንግሃምን ወደ ማንችስተር ይዞ ተጉዟል።
እንደ ማንችስተር ሲቲ ሁሉ በመጀመሪያው ጨዋታ ከባድ ሽንፈት የገጠመው ቼልሲ ከፓሪሰን ዠርማ ጋር የሚያደርገው ጨዋታም የዛሬ ተጠባቂ ፍልሚያ ነው።
በፓርክ ደ ፕሪንስ 5ለ2 ያሸነፈው ፓሪሰን ዠርማ ውጤቱን ለማስጠበቅ ወደ ሜዳ ይገባል።
በሌላ ግጥሚያ በመጀመሪያው ጨዋታ 1ለ1 የተለያየው አርሰናል ባየር ሊቨርኩሰንን በኤምሬትስ ያስተናግዳል።
መድፈኞቹ በሜዳቸው እንደመጫወታቸው ድል አድርገው ሩብ ፍፃሜውን ይቀላቀላሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ከላይ የተጠቀሱት ሦስቱም ጨዋታዎች ምሽት 5 ሰዓት ላይ ይጀምራሉ።
ምሽት 2:45 ላይ ተዓምር እየሰራ የሚገኘው የኖርዌው ክለብ ቦዶ ግሊምት ከስፖርቲንግ ሊዝበን ጋር ይጫወታል።
ቦዶ በሜዳው ያደረገውን የመጀመሪያ ጨዋታ 3ለ0 ማሸነፉ ይታወሳል።
በሸዋንግዛው ግርማ