AMN – መጋቢት 8/2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያ ካሏት ጥንታዊና ታሪካዊ የዜማ መሣሪያዎች መካከል በገና ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል። በተለይም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎት ውስጥ ጉልህ ድርሻ ያለው ይህ መሣሪያ፣ ከአቢይ ጾም ወቅት ጋር ልዩ ቁርኝት እንዳለዉ የሃይማኖት አባቶች ይናገራሉ።
የበገና ድምፅ ሲሰማ አእምሮ ይረጋጋል፣ ነፍስም ወደ ፈጣሪዋ ታንጋጥጣለች። ለመሆኑ የበገና አሠራር ምስጢር ምንድነው? ከአቢይ ጾም ጋርስ እንዴት ተቆራኘ? ኤ ኤም ኤን የሲሳይ በገና ማሰልጠኛ መስራች ከሆኑት ከሊቀ ልሳናት መምህር ሲሳይ ደምሴ ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ቆይታ አድርጓል።
እንደ መምህር ሲሳይ ገለጻ፣ በገና ሙሉ በሙሉ ከተፈጥሯዊ ነገሮች (ከእንስሳትና ዕፅዋት ተዋጽኦ) የሚሠራ የክር መሣሪያ ነው። እያንዳንዱ የበገና ክፍልም የራሱ የሆነ ጥልቅ መንፈሳዊ ምሳሌነት አለው፡፡
በገና በአቢይ ጾም ወቅት በስፋት የሚደመጥበት ምክንያቶች ያሉት ሲሆን ዋናው ምክንያት ስነ-ልቦናዊ ነው። ሰው ሲጾም ወደ ውስጥ መመልከትና ስለ ነፍሱ ማሰብ ይጀምራል። የበገና ድምፅ የሰውን አራቱን ባሕርያተ ሥጋ (እሳት፣ ውኃ፣ መሬትና ነፋስ) በማረጋጋት ለተመስጦ ምቹ ያደርጋቸዋል።
በገናን ከሌሎች የክር መሣሪያዎች ለየት የሚያደርገው “መንዚራው” ነው። ክሩ ከተመታ በኋላ የሚፈጥረው “ጥዝ ጥዝ” የሚል የመንዘር ድምፅ ለየት ያለ መንፈሳዊ እርካታን ይፈጥራል።
በአሁኑ ወቅት በገናን ለመማር ያለው ፍላጎት እየጨመረ መጥቷል። በሥልጠና ማዕከሉ ያገኘናቸው ወላጆች ልጆቻቸው ፈጣሪያቸውን እያመሰገኑና እየተረጋጉ እንዲያድጉ ወደ በገና ትምህርት ቤት ይዘዋቸው እንደሚመጡ ገልጸዋል።
በፍሬሕይት ብርሃኑ