AMN መጋቢት 7/2018
በኢትዮጵያ በቅርቡ የጸደቀው አዲሱ የቱሪዝም ፖሊሲ ለኪነ ጥበብ ቱሪዝም ትኩረት በመስጠት ለብዝሃ ቱሪዝም ዕድገት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን የቱሪዝም ሚኒስቴር ገለጸ።
በሰዓሊ ተገኔ ቁንቢ በጣሊያን ቬንስ በሚካሄደው 61ኛው የቬኒስ ቢየናሌ የኢትዮጵያን ፓቪሊዮን “የዝምታ ቅርጾች” የተሰኘ አውደ ርዕይ ዙሪያ የቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን እና የኤግዚቢሽኑ አዘጋጅ ሰዓሊ ተገኔ ቁንቢ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ የምትሳተፍበት የቬኒስ ቢየናሌ በዓለም ላይ ካሉ ጥንታዊና ታዋቂ ዝግጅቶች አንዱ ነው።
በኢትዮጵያ ከለውጡ ወዲህ ለብዝሃ ቱሪዝም ዘርፍ ትኩረት በመስጠት አዳዲስና ነባር የቱሪዝም መዳረሻዎችን የማስፋፋት ስራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።
ቱሪዝም ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የሚኖረውን አበርክቶ ማሳደግ የሚያስችል የቱሪዝም ፖሊሲ መፅደቁንም ገልጸዋል።
አዲሱ የቱሪዝም ፖሊሲ ብዝሃ ቱሪዝምን ለማሳደግ ታሪካዊና ባህላዊ የቱሪስት መስህቦችን፣ ኢኮ-ቱሪዝም፣ ጂኦ ቱሪዝም፣ የቡና ቱሪዝም፣ ኮንፍረንስ ቱሪዝም እና የአርት/የኪነ ጥበብ ቱሪዝም ዘርፎችን አካቷል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በጣሊያን ቬኒስ ከተማ በሚካሄው ዓለም አቀፍ ዝግጅት የኢትዮጵያ ፖቪሊዮን “የዝምታ ቅርጾች” በማዘጋጀት የኪነ ጥበብ ስራዎቿን የምታስተዋውቅበት መድረክ መሆኑን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው፤ ኢትዮጵያ በኪነ ጥበብ ሥራዎች ባላት ዕምቅ አቅም ልክ ተጠቃሚ አልነበረችም ብለዋል።
ይሁን እንጂ ከለውጡ ወዲህ ባለው የአስር ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ ለኪነ ጥበብ ስራዎች በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ሰዓሊ ተገኔ ቁንቢ ያዘጋጀው አውደ ርዕይ “ዝምታ” የኢትዮጵያን ማህበራዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ የታጠረ ሀይል አድርጎ የሚያቀርብ መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ በስዕልና ቅርፃ ቅርፅ ዘርፍ ያሉ ሰዎች በስፋት እንዲሳተፉ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸው፤ ለሌሎች አርአያ የሚሆን ስኬታማ ስራ ነው ማለታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
“የዝምታ ቅርጾች” አውደ ርዕይ አዘጋጅ ሰዓሊ ተገኔ ቁንቢ የዝምታ ቅርጾች አውደርዕይ ባዶ ሳይሆን በውስጡ የታመቀ ሀሳብ ያለው ነው ብለዋል።